
ከአማራ ፋኖ ብሔራዊ ኃይል (አፋብኃ) የተሰጠ መግለጫ
(የቋራ ቃል ኪዳን)
ግንቦት 01/2017 ዓ.ም
የአማራ ህዝብ የጀመረው የህልውና ተጋድሎ በከፍተኛ ሁኔታ የተጋጋለበት ዘመን ላይ እንገኛለን:: የአማራ ክልልን ጨምሮ በበርካታ የሀገሪቱ አካባቢዎች እየተደረገ ያለው የህልውና ትግል ህዝባዊ መሰረት ያለው በመሆኑ በአንድ ወጥ ድርጅት እየተመራ ባይሆንም አመርቂ ውጤት እያስመዘገበ ይገኛል።
ትግሉ ግለቱን ጠብቆ የበለጠ እንዲፋፋም እና በአጭር ጊዜ የአማራን ህዝብ ነፃነት ያረጋግጥ ዘንድ ይህንን ትግል የሚያቀናጅ እና የሚያስተባብር የጋራ አመራር ያለው ድርጅት መወለድ ግዜው የጠየቀው አንገብጋቢ ጉዳይ ሆኖ ተገኝቷል። ይህንን አንገብጋቤ ጥያቄ ለመመለስ በርካታ ሙከራዎች ተደርገዋል፥ ብዙ ውጣ ውረዶችም ታልፈዋል።
በመጨረሻም የአማራ ህዝብ የናፈቀው፣ ሀገር ወዳድ ኢትዮጵያዊ ሁሉ የተመኘው፣ መላው የፋኖ ሰራዊት የጠበቀው፣ ታሪክ እንዲፈፀም የጠየቀው ጉዳይ ተጠናቋል። የአማራ ፋኖ በጎጃም፣ የአማራ ፋኖ በወሎ (ቤተ – አማራ)፣ የአማራ ፋኖ አንድነት በጎንደር እና የአማራ ፋኖ በሸዋ ከፍተኛ አመራሮች በጋራ ቋራ-ጎንደር ባደረጉት ቀናትን የወሰደ መስራች ጉባኤ ዛሬ ግንቦት o ቀን 207 ዓ.ም የአማራ ፋኖ ብሔራዊ ኃይል (Amhara Fano National Force) የተሰኘ ድርጅት መመስረታቸውን ለመላው ሰራዊታችን፣ ለአማራ ህዝብ እና ለትግሉ ደጋፊዎች እናበስራለን። መላው የትግላችን ደጋፊዎች እንኳን ደስ አላችሁ፡፡
የአማራ ፋኖ ብሔራዊ ኃይል በአማራ ብሔርተኝነት የፖለቲካ ርዕዮት ዓለም ላይ የቆመ ህዝባዊ ተጋድሎ የሚመራ ሲሆን የድርጅታችን ዋነኛ ተልዕኮም እየተደረገ ያለውን የህልውና ትግል እና ህዝባዊ አብዮት ማስተባበር እና ማቀናጀት ይሆናል። ድርጅታችን የአማራ ፋኖ ብሔራዊ ኃይል በኢትዮጵያ ሉዓላዊትና አንድነት ላይ የማያወላውል አቋም ያለው ሲሆን የአማራ ህልውና የሚረጋገጠውም ከሌሎች ኢትዮጵያውያን ኃይሎች ጋር በሚደረግ የጋራ ትግል የአብይ አህመድን የሽብር አገዛዝ በማስወገድ በምትኩ በሽግግር ሂደት በሚገነባ የጋራ መንግስት ምስረታ እንደሆነ ያምናል።
ድርጅታችን የአማራ ህዝብ ተጋድሎ የህልውና ተጋድሎ ነው ስንል ህልውናችንን የተፈታተነውን መዋቅር እና ትርክት መለወጥ እንደሆነ በፅኑ እንደማመናችን መጠን የወልቃይት፣ ጠለምት እና ራያን ጨምሮ በሁሉም የሀገራችን አካባቢ ያለ የወሰን፣ የማንነት እና ራስን በራስ የማስተዳደር ጥያቄ ለማስመለስ እንደሆነ እናረጋግጣለን፡፡
መዋቅራዊ ጥቃትን መቀልበስ እና ለአማራ ህዝብ ማህበራዊ ፍትህን የሚያሰፍን ስርዓተ-መንግስት መፍጠርን ታሳቢ ያደረገውን ትግል የሚመራ ማዕከላዊ አመራር መፈጠሩ የህልውና ትግል እያደረገ ላለው ህዝብ ተጨማሪ አቅም ነው፡፡ ድርጅታችን በሙሉ አቅሙ ትግሉን እንዲመራ የሁሉንም ባለድርሻ አካላት ድጋፍ ይፈልጋል።
የአማራ ፋኖ ብሔራዊ ኃይል አወቃቀር ጠቅላላ ጉባኤ፣ ማዕከላዊ ምክር ቤት፣ የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ እንዲሁም የአባት አርበኞች ምክር ቤትን አካቶ ሕገ ደንብ በማፅደቅ ተቋቁሟል። የአባት አርበኞች ምክር ቤትን አርበኛ መሳፍንት ተስፉ እንዲመሩት መስራች ድርጅቶቹ ተስማምተዋል።
የድርጅቱን አመራር በተመለከተ፦
የመስራች ድርጅቶችን አባላት እና ሰራዊት ለማዋሃድ ጊዜ በማስፈለጉ፤ የድርጅቱን አመራር በማዋቀር ሂደት የመስራች ድርጅቶችን አመራር እና አባላትን ተሳትፎ ከፍ ለማድረግ ሲባል፤ የትጥቅ ትግሉ ከሚደረግበት የቀጠና ስፋት አንፃር የጋራ አመራር በማስፈለጉ፤ እንዲሁም ሌሎች በኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ የፋኖ አደረጃጀቶች የድርጅቱ አካል የሚሆኑበትን እድል ለመፍጠር ሲባል ድርጅቱ በማዕከላዊ ኮማንድ እንዲመራ ተወስኗል። በመሆኑም 13 አባላት ያሉት ማዕከላዊ ኮማንድ የተቋቋመ ሲሆን አባላቱም
1ኛ. አርበኛ ዘመነ ካሴ
2ኛ. አርበኛ ሐብቴ ወልዴ
3ኛ. አርበኛ ምሬ ወዳጆ
4ኛ. አርበኛ ደሳለኝ ሲያስብ ሸዋ
5ኛ. አርበኛ አስረስ ማረ ዳምጤ
6ኛ. አርበኛ ሔኖክ አዲሴ
7ኛ. ጀነራል ተፈራ ማሞ
8ኛ. አርበኛ ዝናቡ ልንገረው
9ኛ. አርበኛ ድርሳን ብርሃኔ
10ኛ አርበኛ አስቻለው በለጠ
11ኛ. አርበኛ ሳሙኤል ባለእድል
12ኛ. አርበኛ ማርከው መንግስቴ
13ኛ. አርበኛ አከበር ስመኘው
ሙሉ የአመራር ምደባ ተሰርቶ እስኪጠናቀቅ ማዕከላዊ ኮማንዱ የድርጅቱን የፖሊት ቢሮ እና የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ሚና በመውሰድ የድርጅቱን ወታደራዊ፣ ፖለቲካዊ፣ የዲፕሎማሲ እና የአስተዳደር ስራዎች እንዲመራ እና እንዲወስን ስምምነት ላይ ተደርሷል። ለመላው የአማራ ህዝብ፤ ለመላው የፋኖ አባላትና አመራሮች በድጋሚ እንኳን ደስ ያላችሁ እያልን የሚከተለውን ጥሪ እናስተላልፋለን።
ለመላው የአማራ ህዝብ
አሁን የአማራ ፋኖ ትግል ወታደራዊ አቅም፣ ፖለቲካዊ ልምድ እና ሁሉን አቀፍ አቅም ወደ አንድ ቋት ተሰባስበው ጠላትን የሚያንኮታኩቱበት ወርቃማ ዘመን ላይ ደርሰናል። ከዚህ በኋላ ይህ ግዙፍ አቅም ተዓምር ሰርቶ የድላችን ጊዜ ቅርብ መሆኑን በድፍረት እና በኩራት መናገር ይቻላል። ይህ እውን ይሆን ዘንድ መላው ህዝብ በብሔራዊ ኃይሉ ሰብሳቢነት የሚመራውን ተጋድሎ በማንኛውም መልኩ በመደገፍ ከጎናችን እንዲቆም ጥሪ እናስተላልፋለን።
ለመላው የአማራ ፋኖ ሰራዊት
ዘመን እና ታሪክ ግድ ብሎት ከረጅም ምጥ በኋላ የተወለደው ድርጅታችን መስዋዕትነት የምትከፍሉለትን ትግል ከግብ ለማድረስ ተገቢውን ትጋት የሚያደርግ ሲሆን በቀጣይ የምንሰጣችውን መመሪያዎች ለመፈፀም እና የትግል ጥሪዎችን ለመቀበል የወትሮ ዝግጁነት እንዲኖራችሁ እናሳስባለን።
ለአክቲቪስቶች፣ ጋዜጠኞች እና ትግሉን ለምትደግፉ የሚዲያ አካላት
ውድ እህትና ወንድሞቻችን! ከመነሻው የአንድ መከረኛ ህዝብ ልጆች ነን! የአንድ አፈር አፈሮች ነን። እኩል የትግሉ ባለቤቶችም ነን። ይህን እንገነዘባለን። የህዝባችን መከራ ከእኛ እኩል እንደሚያማችሁ፥ ከዚህ መውጫ መንገድ ፍለጋውም እኩል እንደሚያስጨንቃችሁ እናውቃለን። ሚዲያ ወሳኙ የትግል ግንባር ነውና በተሰለፋችሁበት ግንባር የነበራችሁንና ያላችሁን ሚናም በቅጡ እንረዳለን፡፡ ይሁንና ከመጓጓት፥ ከበጎ ጭንቀትም ይሁን ከግለሰብና ቡድናዊ ፍላጎትና ተልእኮ የተነሳ የሚደረጉ ገደብ የለሽ ጣልቃ ገብነቶችና የተዛነፉ ትንተናዎች ትግሉን እያወኩት መሆኑን በመገንዘብ ማናችም የሚዲያ ስራዎች የመታገያ ተቋም ፈጥሮ፣ ህዝባችንን ለአንድ አላማ በአንድ ላይ ማሰለፍን ታሳቢ አድርጎ የህልውና ትግሉን ማሸነፍን ማዕከል ያደረገ እንዲሆን የበኩላችሁን ድርሻ እንድትወጡ እናሳስባለን!
ለዳያስፖራ ወገኖቻችን
የህልውና ትግሉ አሁን ያለበት ደረጃ ይደርስ ዘንድ የአማራ ዳያስፖራ የነበረው ሚና በትልቁ የሚገለፅ ነው፡፡ ሆኖም ወጥ የሆነ የዳያስፖራ አደረጃጀት አለመኖሩ እና ተመሳሳይ ግብ እና ዓላማ የሌለ በሚያስመስል ደረጃ ያሉት የእርስ በእርስ ንትርኮች በዳያስፖራው ብቻ ሳይሆን በፋኖ አደረጃጀቶች ላይ ያለው አሉታዊ ተፅዕኖም በቀላሉ የሚገለፅ አይደለም። በመሆኑም የዳያስፓራው ማህበረሰብ በአንድነት እንዲደራጅ እና ትግሉን እንዲደግፍ ጥሪ እያደረግን በዚህ ረገድ ድርጅቱ የሚወስደውን ኃላፊነት ወስዶ ወደ ተግባር እንደሚገባም እናሳውቃለን፡፡
ከብሔራዊ ኃይሉ ውጭ ላላችሁ የፋኖ አደረጃጀቶች
በድሮን እና በጅምላ ጨራሽ መሳሪያወች እየተጨፈጨፈ ያለው የአማራ ህዝብ የእኛን አንድነት በፅኑ ይፈልጋል፤ ሁሉም አፈሙዞች ወደአንደኛ ጠላት ብቻ መነጣጠር እንዳለባቸው የአማራ ፋኖ ብሔራዊ ኃይል ያምናል፤ ለሁላችን እድል የሚሰጥ በልካችን የሚያስተናግደን ሰፊ አዳራሽ ፈጥረናል። ስለሆነም ያለምንም ማመንታት ድርጅቱን እንድትቀላቀሉ ጥሪ እናቀርባለን።
ለአገዛዙ ካድሪዎች፣ የሰራዊቱ መኮንኖች እና ወታደሮች
ይህ ትግል የህዝብ ትግል ነው፣ ማሸነፋችንም የተረጋገጠ ጉዳይ ነው። የአብይ አህመድን አገዛዝ በማገልገል ጥቁር ታሪክ እየፃፋችሁ ነው፡፡ የአማራ ፋኖ ብሔራዊ ኃይል የግለሰብን ስልጣን ሳይሆን የህዝብን ነፃነት አስቀድመው ለሚመጡ ወገኖች በቂ የመታገያ ሜዳ ለመፍጠር ዝግጁ ነው። ስለሆነም ትግሉን እንድትቀላቀሉ እና የማይቀረውን የድል ፅዋ አብረን እንድናነሳ ጥሪ እናቀርባለን።
ለመላው ኢትዮጵያዊያን
የአማራ ህዝብ የህልውና ተጋድሎ የኢትዮጵያን ህልውና የማይፈታተን ይልቁንም በጋራ ትግል በሚያምን አታጋይ ድርጅት የሚመራ ነው። የአብይ አህመድ አገዛዝ የሽብር ተግባሩ ዒላማ ያደረጋቸው በርካታ ወገኖች መኖራቸውም የታወቀ ነው፡፡ ስለሆነም መላው ኢትዮጵያዊያን ይህንን የህልዉና ትግል በመደገፍ ከህዝባችን ጎን እንድትቆሙ ጥሪ እናቀርባለን።
በፀረ ብልጽግና ትግል ላይ የምትሳተፉና ነፍጥ ያነሳችሁ ኢትዮጵያውያን የገጠመን ጠላት የዓለም አቀፍ የጦርነት ህግ የማይገዛው፣ የሞራል ተጠይቅ የሌለው የሀገር ሀብት ለሽብር ተግባር የሚያዉል፣ የሚመራውን ህዝብ ላይ ሽብር በመፍጠር ስልጣን ላይ መቆዬት የሚፈልግ ልፍስፍስ ኃይል ነው:: ስለሆነም በጠላታችን ላይ በጋራ ለምናደርገው ትግል የተቀናጀና የተናበበ ሁለገብ ትግል በጋራ እንድናደርግ ጥሪ እናቀርባለን።
ለዓለም አቀፉ ማሕበረሰብ
በዓለም የጦርነት ታሪክ ተደርጎ በማይታወቅ ደረጃ በራሱ ህዝብ ላይ የሽብር ተግባር እየፈፀመ ያለውን አብይ አህመድ እና አገዛዙ በሀገር ስም የሚደረግለትን ድጋፍ ለጦርነት ማዋል ከጀመረ ሰነባብቷል። አብይ አህመድ በዩናይትድ አረብ ኢሚሬት አስተባባሪነት የአማራን ሕዝብ በድሮንና በጀት እየጨፈጨፈ ያለ ሲሆን የምስራቅ አፍሪካን ቀጠና የጦርነት እና የትርምስ ሜዳ በማድረግም ለቀጠናው ሰላምና መረጋጋት ፀር ሆኖ ቀጥሏል። የአማራ ህዝብ ተጋድሎ በድል ሲጠናቀቅ ይህንን ነባራዊ እውነት የሚለውጥ ውጤት እንደሚያመጣም እሙን ነው። ስለሆነም የአብይ አህመድን አገዛዝ ባለመደገፍና ማንኛውንም ዲፕሎማሲያዊ ጫና በማድረግ ለሰላም እጁን እንዲሰጥ የበኩላችሁን ተፅዕኖ እንድታደርጉ ጥሪ እናቀርባለን::
የአማራ ፋኖ ብሔራዊ ኃይል ማዕከላዊ ኮማንድ
ቋራ – አማራ – ኢትዮጵያ