የፋኖ አቋም ወልቃይት ላይ ምን ቢሆን ይመረጣል?

የፋኖ አቋም ወልቃይት ላይ ምን ቢሆን ይመረጣል?

በአንበርብር ሀይሉ

፩.ወልቃይትና ፋይዳው:

ወልቃይት ለወልቃይቴ፣ ለጎንደር፣ ለአማራና ለኢትዮጵያውያን ፋይዳው ዘርፈ ብዙ ነው። ወልቃይት የምስራቅ አፍሪካ ቁልፍ ስትራተጂክ ቦታም ጭምር ሆኗል።

ወልቃይት አማራው ላይ ባለፈው 50 ዓመት በዕቅድ ለደረሰው ግድያ፣ አፈና፣ ስቃይ፣ መፈናቀል፣… ሁሉ  ጥሩ ማሳያ ናሙና ነው።

የአማራው የህልውና ትግል በዋናነት የተለኮሰው “ወልቃይት ብረሳሽ ቅኜ ትርሳኝ” በሚል የጋራ ማሰባሰቢያ አጀንዳ ነው። ወልቃይት ለአማራው የህልውና ትግል ቀይ መስመር ነው።

ወልቃይት ስንል፣ አንደምታው ሰፊ ነው።  ከወሎ፣ ከጎንደር፣ ከጎጃምና ከሸዋ ክፍለ ሃገሮች ከህግ ውጪ በማን አለብኝነት በጠመንጃ በወያኔ የተወሰዱትን  ራያ፣ መተከል፣ ሸዋ፣…..ማለታችን ብቻ ሳይሆን፣ በሀረርጌ፣ በወለጋ፣ በአርሲ፣ በባሌ፣.. በመላው ኢትዮጵያ ተበትነው እንደ 2ኛ ዜጋ በተለያዩ የአፓርታይድ ባንቱስታን/ክልሎች የሚሰቃዩትን አማሮች/ኢትዮጵያውያን ጭምር ማለታችን ነው።

በታሪካዊው ሀምሌ 5 ቀን የወልቃይት ማንነት አስመላሽ ኮሚቴ ሰብሳቢ ኮ/ል ደመቀ፣ ወደ ትግራይ አፍነው ሊወስዱት ጎንደር ድረስ የመጡትን በአድዋ ገዢ መደብ የተሰማሩትን የወያኔ ነፍሰ ገዳዮች፣ “እጄን እልሰጥም” ብሎ በጀግንነት መጋደሉ፣ የአማራውን የህልውና ትግል አብሪ ጥይት ተኩሷል። የወያኔን ቆሌ በመግፈፍ፣ የወያኔን የመጨረሻውን መጀመሪያ አሳይቷል። ኮ/ል ደመቀ ዳግማዊ ቴድሮስ በመሆን የአማራውን “ግፍ በቃኝ” ብሎ መነሳት አብስሯል። አማራው ከፈጣሪው በታች መዳኛው ነፍጡ እንደሆነ በተግባር ለወዳጅም ለጠላትም አሳይቷል። የህልውና ትግሉን እንደ ሰደድ እሳት አቀጣልሏል።

፪. ወልቃይት ኮ/ል ደመቀ ዘውዱ እጅ መቆየቱ  ጥቅሙ

በዘመነ ወያኔ በጊዜው የመከላከያ የአደጋ ጊዜ ተጠሪ በነበረው የአማራ ልዩ ኃይል ቅራቅር ላይ ወደ ሸዋ ሊያደርግ የነበረው ግስጋሴ ተቀልብሶ፣ ወልቃይት ነጻ ከመውጣቱ በፊት፣  አማራው በወልቃይት ይሳደድ፣ ይገረፍ፣ ይገደል፣ ይፈናቀል ነበር። አማራው በቋንቋው መማር፣ መዳኘት፣ መምረጥ፣ መመረጥ አይችልም ነበር። አማርኛ ቋንቋ መናገር፣ ሰርግ ላይ የአማርኛ ዘፈን ማዘፈን፣ የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ መያዝ፣ የፋሲል ከነማን ማልያ መልበስ፣ ….ያስገርፍ ያሳስር፣ ያስገድል ነበር።

አሁን  በኮ/ል ደመቀ ዘመን አማራው በደሙ እራሱን በራሱ ማስተዳደር፣ በቋንቋው መማር፣ በቋንቋው መዳኘት፣ መምረጥ፣ መመረጥ፣ የኢትዮየያን ሰንደቅ ዓላማ መያዝ፣ በአማርኛ መናገር፣ መዝፈን፣ ….በነጻነት ጀምሯል።

የተከዜ ዘብ( የፋኖ እርሾ በወልቃይት) ያለማቋረጥ መሰልጠንን ፋኖ ሊደግፈው ይገባል። አማራው ፋኖን አሰልጥኖ አስታጠቀ፣ በተከዜ ዘብ ስም ሰልጥኖ ታጠቀ፣ ልዩ ኃይል/ አድማ በታኝ ተብሎ ሰልጥኖ ታጠቀ፣ መከላከያ ውስጥ ገብቶ ሰልጥኖ ታጠቀ፣ ……ዋናው ቁምነገሩ መሰልጠኑ፣ መታጠቁ፣ መደራጀቱ፣  ከደምመላሽ ጠመንጃው ጋር ዳግም መገናኘቱ ነው። የቁርጥ ቀን ሲመጣ የዘመኑ አክሊሉ ኃብተወልዶች ሲፈጠሩ  ይሄ ሁሉ ሰልጥኖ ታጥቆ የተቀመጠው ኃይል ለአማራው ብሎም ለኢትዮጵያ  ህልውና በቅንጅት እንዲሰራ ማድረግ ይቻላል።

ኮ/ል ደመቀ አንድ ወቅት ላይ በአጽንኦት እንደገለጸው፣ ከአሁን በኋላ ወልቃይትን ይዘን የሚከፈለውን መስዋዕትነትን ከፍለን በራሳችን እጅ እንዲቆይ  እናደርጋለን እንጂ፣ ዳግም በወያኔ እጅ እንዲገባ ፈቅደን አናለቅስም ብሏል።

ወያኔ ደግሞ ደጋግሞ በእብሪት ወልቃይት ላይ የቃጣውን ወረራ፣ ወያኔን ከማንም በላይ ጠንቅቆ በሚያዉቀው፣ የአማራውና የኢትዮጵያ ኩራትና ደምመላሽ  በሆነው የተከዜ ዘብ ተመክቶ፣ የወያኔን ፍላጎት ቅዠት አድርጎታል።

የኦሮሙማንና የወያኔን ጫናና ሸር ከመቋቋም ባሻገር፣ የፌዴራል በጀት እስከ አሁን ድረስ በኦሮሙማ በሴራ ብትከለከልም፣  በጀት ከማንነት አይበልጥም በማለት፣  ወልቃይት አሁን ላይ የታሪካዊ ባለቤቱ የጎንደር ጠቅላይ ግዛት አካል ሆና  እየተዳደረች ነው።

፫. የተከዜ ዘብ ቀይ መስመር

ወልቃይት  በጎንደር ስር የቆየችው፣  የኮ/ል ደመቀ የተከዜ ዘብ ቅሬታውንና ልዩነቱን በሆዱ ይዞ፣ ከአብይ ጋር ፊት ለፊት ለጊዜውም ቢሆን ባለመጋጨቱ ነው። ይሄ እንደተጠበቀ ሆኖ ለተከዜ ዘብ ዋናው ቀይ መስመር መሆን ያለበት፣ ወልቃይትን የባለቤቱ የጎንደር አካል አድርጎ ማቆየት፣ ፋኖን  በአደባባይ ማመስገን ባይችሉም፣ በአብይ ተጽዕኖም ቢሆን ፋኖን ከማውገዝ ከማጥላላት መቆጠብ ነው። የተከዜ ዘብ ይሄን በጥንቃቄ እስከ አሁን ድረስ እያደረገ ነው።

ነገሮች ሲለወጡ፣ ይሄ ታጥቆ ሰልጥኖ የተቀመጠ የተከዜ ዘብ በአንድ ጀምበር የወልቃይት ፋኖ እርሾ መሆኑ አይቀሬ ነው።

በእርግጥ በፋኖ ስም ወልቃይት ውስጥ የተከዜ ዘብ ላይ ውጊያ በተደጋጋሚ የከፈተ ኃይል አለ። ይሄ ቡድን ማነው? ፍላጎቱስ ምንድነው?

ፋኖና የተከዜ ዘብ እርስ በእርስ ቢዋጉ፣ በዋናነት የሚጠቀሙት ወያኔና የኦሮሙማ  ኃይል ነው። ወያኔ በተደጋጋሚ ወልቃይትን ለመያዝ ያደረገው ወረራ በአስተማማኝ ስለተቀለበሰ፣ የቀረው አዋጪ የድብቅ ስትራተጂ ፋኖና የተከዜ ዘብ በሰርጎ ገቦች አማካኝነት ወንድም ወንድሙ ላይ ዘምቶ እንዲዳከሙ በማድረግ፣ ወልቃይትን ዳግም በቀላሉ ወሮ ለመያዝ ነው። እኒህ በፋኖ ስም የወያኔን አጀንዳ የሚያራምዱ የዘመናችን ዋለልኝ መኮንኖች/ ሰርጎ ገቦች በጎንደር ልጆች በሚገባ ይታወቃሉ።

ሌላው ወንድም ወንድሙ ላይ ጦር እንዲሰብቅ ደም እንዲቃባ የሚያበረታታው፣  ወልቃይት ላይ የሚሸረበው የፓለቲካ ሴራ የማይገባው፣ የፓለቲካ የዋህ፣ በስሜት የሚነዳ ደጋፊ ነው።

ለማንኛውም እውን ፋኖ መታገያ ግንባር እና  የሚዋጋበት ሜዳ አጥቶ ነው ወልቃይት ውስጥ ገብቶ ከወንድሞቹ ጋር ደም መቃባት የሚፈለገው? ምን ትርፍ ለማምጣት? ማንን ለመጥቀም? ደግሞስ፡ የዚህ ፋኖ ሃይል እና የተከዜ ዘብ ጦርነት ቢፋፋም፡ ትህነግ ጦርነቱን ተቀላቅሎ የተከዜን ዘብ ከኋላ በማጥቃት የሚመኘውን ለማሳካት መሞከሩ ይቀራል? እንዴት እንዲህ እንደዋዛ ለትህነግ ፈር ቀዳጅ የሆነ ጦርነት ለመጀመር ይታሰባል?

ሲሆን ሲሆን ፋኖ ወልቃይትን ለወንድሞቹ ለተከዜ ዘብ ትቶ፤ ከተቻለ ጎንደርን፣ ደሴን፣ ባህርዳርንና ደብረ ብርሃንን ቢይዝ አይመረጥም?

ፋኖ ወልቃይትን ከተከዜ ዘብ ቢረከብ እንኳን፣ አሁን ባለው አቅም ለምን ያክል ጊዜ ከአብይ መከላከያ ጠብቆ በእጁ ያቆያል? መከላከያ እጅ ደግሞ ከወደቀ፣ ኦርሙማ ወልቃይትን መልሶ ለወየኔ እንደማይሰጠው ምን ማስተማመኛ አለ? ቀይ መስመራችን እስክልተጣሰ ድረስ ወልቃይትን በእጃችን ይዘን ማቆየቱ ይሻላል፣ ወይስ በንኅዝላልነት ከእጃችን እንዲወጣ ማድረግ?

፬. የወልቃይት ጦርነት አይቀሬ መሆኑ

“ለሁሉም ጊዜ አለው” እንደሚባለው፣ ወያኔና የትግራይ ህዝብ አንድ ናቸው የሚለው የስብሃት ነጋ ተረት ተረት አሁን በትግራይ ህዝብ ዘንድ ተቀባይነት እያጣ ነው። ወያኔ እንደ አዲስ ፓርቲ አልመዘገብም ብሏል። ወያኔ ለ2ኛ ጊዜ  በምርጫ ቦርድ ህጋዊነቱ አክትሟል።

በራያው በጌታቸው ረዳ ሊመሰረት የታሰበው የትግራይ ሊብራል ፓርቲ የወያኔን ደጋፊ ለሁለት ይከፍለዋል። በወያኔ መፈንቅለ መንግስትና ጥቆማ ወደፊት የመጣው ታደሰ ወረደ አቋም የለሽ ግለሰብ በመሆኑ፣ ከወያኔ ይልቅ ለአብይ እንደሚያድር ከአሁኑ ፍንጭ በመገኘቱ፣ በወያኔ ከሃዲ ተብሎ መወገዝ ጀምሯል።

የደብረጽዮን ቡድን ፓለቲካና ወታደራዊ አመራሮች፣ አስክቲቪስቶች ኤርትራ ድረስ በመሄድ እየዶለቱ እንደሆነ ተዘግቧል።  ቀኑን፣ ቦታውን ተሳታፊዎች ሳይቀር በስም ተጠቅሰው በሰፊው ተዘግቧል። የክፉ ቀን ሲመጣ በዋናነት ኤርትራን የደብረጽዮን ቡድን ማፈግፈጊያ ለማድረግ እንዳሰበ ይገመታል።

የወያኔ ከኢሳያስ ጋር መሞዳሞድ፣ የታደሰ  ወረደ ወደ አብይ ጉያ ለመግባት የሚያሳየው ፍንጭ፣ የደብረ ጽዮንን የወያኔ ፍንካች ከታደሰ ወረደ ጊዝያዊ አስተዳደር  ስልጣንና ሃብት ያርቀዋል።

የትግራይ ህዝብ በዘመነ ወያኔ ታሪኩ  እንደ አሁን ተከፋፍሎም ግራ ገብቶትም አያውቅ። የደብረጽዮንና የጌታቸው ረዳ ቡድን በመባባል ህዝቡ ለ2ት ተሰንጥቋል። የደብረጽዮን ቡድን ከሻዕቢያ ጋር ለመስራት መወሰኑ፣ ቀላል የማይባል የትግራይ ህዝብን አስቆጥቶ የወያኔ ተቃዋሚ አድርጓል። በራያው ልጅ በጌታቸው ረዳ በአድዋው ቡድን በእነ ደብረጽዮን በመፈንቅለ መንግስት መባረሩ፣ በጌታቸው ረዳ ጊዜ የተዋቀረው የራያ ጊዝያዊ አስተዳደር እራሱን እንደማያፈርስ ለታደሰ ወረደ ገልጿል። ትግራይ ውስጥ ያሉ ተቃዋሚ ፓርቲዎች በሙሉ የታደሰ ወረደ ጊዝያዊ አስተዳደርን፣ የደብረ ጽዮን ቡድን ስለተቆጣጠረው ተቀባይነት የለውም ብለው ተቋውሟቸውን ገልጸዋል።

የአብይ ቂመኛነት እንደተጠበቀ ሆኖ፣ አብይ በተለይ ወያኔ ላይ የቋጠረው ቂም ወያኔ ከሻዕቢያ ጋር መስራት መጀመሩ፣ ጊዜው አሁን ነው በማለት ወያኔን መቀመቅ ከመክተት ወደ ኋላ አይመለስም። የሰሞኑ የጌታቸው ረዳ በፋና ላይ የሰጠው  ሰፊ ኢንተርቪው የዚህ የአብይ ወያኔን የመቅበር ስትራተጂ አካል ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል።

ወያኔ ይሄን ሁሉ ከሁሉም አቅጣጫ የመጣበትን ተቃውሞ ለማስቀየስ፣ አብዛኛው የትግራይ ህዝብን ከጀርባው ለማድረግ፣ ወልቃይትን ለመውረር መሞከሩ አይቀሬ ነው።

፭. መደምደሚያ

የወልቃይነት ጦርነት አይቀሬ ነው። በወልቃይት ትልቅ ቀጠናዊ ጦርነት የመካሄድ ዕድሉ የሰፋ ነው። ወያኔ ቀድሞውኑ ወልቃይትን ለመውረር ሱዳን እየቀለበ ያስቀመጠው አርሚ፣ አሁን ላይ  የአልቡሁራን መንግስት ቅጥረኛ ተዋጊ ሆኖ ይበልጥ የልብ ልብ ተሰምቶታል። ሱዳንም ቢሆን በአወዛጋቢው የአል ፋሽጋ ለም መሬት ጋር በተያያዘ ወልቃይትን በወያኔ በማስወረር የአማራውን ኃይል ማዳከም መፈለጓ ጥርጥር የለውም። በወያኔና በሻዕቢያ መካከል ያለውን የቆየ መከዳዳት ላጤነ፣ ወያኔ ወልቃይትን ከከበባ መውጫ መሬት ለማድረግ መሞከሩ አይቀሬ ነው። የግብጽም እጅ ከወያኔና ከሻዕቢያ ጀርባ በወልቃይት ዙርያ ይኖራል።

ስለዚህ ፋኖ እርስ በእርሱ ( ፋኖና የተከዜ ዘብ) የሚዋጋበት ጊዜም ምክንያትም ሊኖረው አይገባም። ፋኖ ያለውን ሃይል አሰባስቦ ወደ አዲስ አበባ ከመገስገስ ይልቅ ወደ ወልቃይት ሄዶ መዋጋት የሚኖርበት ጊዜ ቀይ መስመራችን ሲጣስ ብቻ መሆን አለበት። ወልቃይት ላይ ወያኔ ወረራ ሲጀምር ወይም አብይ ወልቃይትን ከተከዜ ዘቦች እጅ ወስዶ እኔ ላስተዳድር ወይም ለወያኔ እንደ ገጸ በረከት መስጠት ሲጀምር።

በመጨረሻም በፋኖ ስም  ከማንም የውጭም ይሁን የውስጥ ኃይል  ጋር የሚደረግ ውይይት፣ ድርድርና ወዳጅነት፣  የመጀመርያው ቅድመ ሁኔታ ወልቃይት የጎንደር ክፍለ ሀገር አካል መሆኗን በግልጽ ካለምንም ብዥታ መቀበል ነው። ወልቃይት የፋኖ ቀይ መስመር ነው።

guest

0 Comments
Oldest
Newest Most Voted
Inline Feedbacks
View all comments

0
Would love your thoughts, please comment.x
()
x