
የኢትዮጵያና ቻይና የ50 ዓመት ጉዞ፡ እኛ ወደ ፍጀት እነሱ ወደ ብልጽግና
በያሬድ ኃይለመስቀል
“ጨቋኝ ማነው፤ መንግስት የሚባል ምናባዊ ሰው ወይስ እኛ፡ የጭቆና መሳሪያዎች እኛ ነን። ስለዚህ ወታደር ከሆኑ ተኩሶ በመግደልና በመሳት መሀከል ያለው ህሊና ነው። ታዝዤ ነው አትበል። ውሸት ነው። ፓሊስ ከሆንክ ሰው በመግረፍና በማጉላላትና የታሳሪን መብት በማክነር መሀከል ያለው ህሊና ነው። ሚሊሽያ፤ ልዩ ሃይል፤ ደንብ አስከባሪ፤ ዘበኛ፤ ትራፊክ፤ ገቢዎች፤ የመንግስት ንግድ ቢሮ፤ ኢሚግሬስን ሆነህ የህዝብን መብት እየገፈፍክ ተጨቆንኩ አትበል። እንደውም ይበልህ ነው የሚይስድብልው። እራስህ ጨቋኝ ሆነህ መብት ይገባኛል አትበል። መጀመሪያ ከጨቋኝነት እራስህ አጽዳ።”
የሀምሳ አመት የኢትዮጵያና ያቻይና ጉዞ
ኢትዮጵያ የዛሬ 50 ዓመት የነብረችበት ቦታ ነች ያለችው። ከአለም በድህነት ከ193 ሀገራት 180ኛ ሀገር ናት። እነ ደቡብ ሱዳን፤ ብሩንዲ የመሳሰሉት ከታች ባይደግፏት ኖሮ የመጨረሻዋ ሀገር እንሆን ነበር። ሌላው ቻይና ከኛ ጋር ተመሳሳይ ገቢ የነበራት ሀገር ነበረች፣ እኛ ስንገዳደል እሷ የአለም ሁለተኛዋ ሀብታም ሀገር ሆናለች። እስቲ ረጋ ብለን እናብበውና እንወያይበት።
የኢትዮጵያ ችግር ከድጡ ወደ ማጡ መሄዱ ለቀባሪው ማርዳት ነው። ላለፉት 50 ዓመታት ችግሩ ይቃለላል ብለን ስናስብ እየተባባሰበት ነው የሄደው። እኔ እድሜዬን በሙሉ የነበሩትን ስራዓት ሳወግዝ ነው የኖርኩት። ኮለኔል መንግስቱ፤ መለሰ ዜናዊ፤ ኃይለማሪያም ደሳለኝ፤ አብይ አህመድ፤ ሰደድ፤ መሲሶን፤ ደርግ-ኢሰፓ፤ ህውሓት-ኢህአዴግ፤ አሁን ደግሞ ኦፒዲኦ-ብልጽግና እያልኩኝ። ይሁንና እንነዚህ ሰዎች አንድ የሚያደርጋቸው ቁመት፤ ሞያ፤ የቆዳ ቀለም፤ ብሄር ቋንቋ አይደለም። አንድ የሚያደርጋቸው በዚህ ሀገር ስነልቦና ተወልደው ማደጋቸው ነው። እኛስ የዚህ ቫይረስ ተሸካሚዎች ብንሆንስ?
እኛ ለሀምሳ አመታት ቡና እየሸጥን፤ እርዳታ እህል ለምነን ከዛ ሸጥን ክላሽና ገዝተን መገዳደል ከጀመርን ይሄው ሀምሳ አመት ሞላን። ቻይና ደግሞ መገዳደሉን አቁሞ ድሮን ሰርቶ ለኛ ይሸጣል።
የቻይናና የኢትዮጵያ የ50 ዓመት ፓለቲካ ጉዞ
ቻይና የዛሬ 50 ዓመት ከኛ የባሰች ሀገር ነበረች። እኛ የኮረጅነውን አብዮት እነሱም ሞክረውት ወደ 55 ሚሊዮን ህዝብ በረሀብ እንደሞተ ተመዝግቧል። በአብዮታዊ የእርስ በእርስ ጦርነትም ወደ 10 ሚሎዮን የሚገመት ህዝብ ከዛ ደግሞ ጸረ አብዮተኛ አደሀሪ ተብሎ ደግሞ ወደ 2 ሚሊዮን ህዝብ አልቋል። እኛ በ1966 ዓመት አብዮት በጣም ጥሩ ነገር ነው ብለውን ገፍትረን ስንገባ እነሱ ደግሞ አብዮት መጥፎ ነው ብለው በ1968 ዓመተ ምህረት ሸስተው ወጡ።
የኛ የነፍ ወከፍ ገቢ በ1966 ዓመተ ምህረት 134 ዶላር ሲሆን የነሱ ደግሞ 160 ነበር። ልዮነቱ የ26 ዶላር ነበር። አሁን የኢትዮጵያ የግል ገቢ 1000 ዶላር በታች ሲሆን የቻይና ደግሞ $13,500 ገደማ ነው። ልዩነቱ 12ሺ ዶላር ወይንም የኛ 12 ዓመት ገቢ ማለት ነው።
የአጠቃላይ የሀገራቸው ምርትና ግልግልሎት $17.8 ትሪሎዮን /trillion, ሲሆን ይኛ ደግሞ ከ100 ቢሎዮን/ billion በታች ወርዷል። ይ ህ ማሽቆልቆል የመጣው በገንዘብ ግሽበት ፓሊሲ ጭመር ነው። ቻይና የአለም 2ኛ ኢኮኖሚ ነች እኛ ደግሞ 80 ገደማ ነን ምክኛቱም ከኛ በጣም ያናነስይ እንደ ጅቡቲ ያሉ ሀገሮች ብዙ ስለሆኑ፤ ይሁንና ወደ በነፍስ ወክፍ ገቢ ስንሄድ ደግሞ ከ 192 ሀገሮች 180 ላይ ነው እንገኛለን።
የዶንቆሮዎች አብዮት
አብዮትም በእውቀት ካልተመራ ወድቀት ነው። የቻይና ኮሚኒስት ፓርቲና የዮጎዝላቪያ ፓርቲ ለኢትዮጵያ ወታደራዊ ደርጎችን አብዮትን ወደ ኋላ ተመልሰችሁ አትጀምሩ፤ እኛ የሞከርናቸውንና የተሳሳትንባቸውን ነገሮች ተምራችሁ አትድገሙ። ሶሻልሲዝም ያኔ 57 ዓመት እንድሜ ነበረውና ለብዙ ረሀብ ሞት፤ ቀይ ሽብር፤ ነጭ ሽብር ምክንያት ነበር። ስለዚህ በዚህ አላለፉ እሱን አትድገሙ ብለው መክረው ነበር። አይ አይሆንም ብለው የኛ ሰዎች በረሀቡም፤ ሰፈራውንም፤ ቀይ ሽብሩንም፤ ሰው ቀጥሮ ማሳረስንም እንደ ብዝበዛ መደቡት። ያ ጦሙን የሚያደ መሬት እና ስራ አጥቶ የሚራብ ወጣት ፈጠረ። የነበረው የስራ መስክ መሳሪያ ይዞ መዋጋት ሆነ። የኢንዱስትሪ ፓርክ ሳይሆን የሽምቅ ተዋጊ ማሰልጣኛ በየ ቦታው ተቋቋመ።
እንግዲህ እኛ ቻይና የወጣችበትን የረሀብ አብዮት እኛ ተከራይተን ገባንበት። እኛ የግል ሀብትን ሁሉ 1968 እስከ 2917 እየወረስን ስንቀጥል ቻይና ደግሞ በ1968 የግል ሀብት እንዲፈጠር ኢኮኖሚውን ከፈተች። እኛ አድሀሪያንን፤ ጸረ አይዮተኞችን፤ መሀል መንገደኞችን፣ ቀኝ መንገደኞችን፤ ተገንጣዮችን፤ አስገንጣዮችህ፤ ትምክህተኞችን፤ ነፍጠኞችን፤ አማሮችን፤ መጤዎችን፤ ሰፋሪዎችን፤ ሴማውያንን፤ ጁንታን፤ ጃዊሳን መጀመሪይ መጨረስ አለብን ብለውን ስንተጋ የቻይ ደግሞ መገዳደላችን ያብቃ ብላ በ1968 አወጀች። ገዝቶ የሚገዳደል ካለ ክላሽና ቺቺ እንሸጣለን ብለው ፋብሪካ ከፈቱ።
እኛ መጀመሪያ መገዳደል አለብን ስንል ኮሚኒስት ፓርቲ ደግሞ ከአሁን ወድያ ቻይና ቻይናን አይገለም ብሎ ወሰነ። እኛ ወደ 80 እንከፋፈል ልዮነት አለን ስንል እነሱ አንድ ቻይና ፓሊሲ ብለው አወጁ። እንኳን ቻይና ውስጥ ያለውን ቀርቶ ከቻይና ውጪ ያለውን ቻይና የሚመስለው ሁሉ አንድ ነው አሉ። እኛ በመንደር በጎሳ በሀይማኖት ስንል እንሱ የቻይናን መውደድ አንደኛ ሀይማኖት አደረጉት፣ ትምህርታቸው ጥዋት ቻይናን በማሰደስ ማታ ቻይናን በማወደስ ይዘጋል። የእለት ተዕለት ጸሎታቸው የአልመ ገዢ፤ የታፈረች፤ የተከበረች ቻይና መፍጠር ሲሆን እኛ ደግሞ የመንደር ባላባት መሆን ሆነ።
ቻይና ሁላቸንም አንድ ሆነን ከአለም ጋር ተፎካክረን የአለም አንደኛ ኢኮኖሚ፤ አንደኛ ሀይል እንሆናለ እንጂ እርስ በእርሳችን አንጨራረስም ብለው ጀመሩ። እኛ እስካሁን ገድለን አልጨረስንም። አደሀሪ በዝባዝ ብለን የጀመርነው አሁን መጤ፤ ኩሽ፤ ኦሮሙማ፤ ሴማቲክ እያለ በየቀኑ ጠላት ይፈጥራል። እነሱ ግን የታላቋን አሜሪካ ተፎካካሪ ሆነው ይሄው ለኛው አዲስ ጌቶች ሆነው መጡ።
የኛ ችግር ምንድነው
የኛ ችግር ምንድነው ብንል ብንጠይቅ የማሰብና ችግርን የመፍታት አቅማችን ነጸብራቅ ነው። ከላይ እንዳልኩት ከመንግስቱ እስከ አብይ እያወገዝኩ ነው የኖርኩት ይሁንና አንድ ያልገባኝ ነገር እነዚህ ሰዎች የመሀበረሰቡ ስነ ልቦና ውጤቶች ናቸው። የማሰብ ችሎታቸው ደካማ መሆኑ ያው የሚያሳየው የኛንም ድክመት ነው። ጭካኔውም ቢሆን መንግስቱ ተኩሶ የገደለው ሰው አንዳለ አልሰማሁም። ግን ስርአት ለማገልገል ጎረቤት ጎረቤቱን አብዮት ጠባቂ ሆኖ፤ ወታደር ሆኖ፣ ፓሊስ ሆኖ፤ ሚሊሽያ ሆኖ፤ ልዩ ኃይል ሆኖ፤ ደህነት ሆኖ የሚያገለግል የሚገል ሰው በሚሊዮን የሚቆጠር አለ።
እራሱ ረሀብተኛ ሆኖ ለምን ዶክተር መብቱን ይጠይቃል ብሎ የሚያሽቃብጥ አለ፤ እራሱ ረሀብተኛ ሆኖ ደንብ አስከባሪ ብለው ሲደልሉት ጉሊት ላይ ሽንቁርትና ቅመም የምትሸጥ እናትን ብቅሏን የሚበትን፤ በጥፊ የሚያጠናፍር ደንብ አስከባሪ ሞልቷል። በዚህ አይነት ሁኔታ ውስጥ ታድያ እነዴት ስርአት ባቻ ማማረው ይጠቅማል።
የተጨቋኝ ተጨቋኝ ሀገር
የተጨቋኝ ተጨቋኝ ሀገር ሆኖ ሳለ እኛ እጃችንን ታጥበው የዚህ የራሳችን ድህነትና የጭቆና መሳሪያ መሆናቸንን ካልተረዳን እንዴት ከጭቆና እንወጣለን።
ስለዚህ በኛ ውስጥስ የተደበቁ ትናንሽ አብይ፤ መለስ፤ መንግስቱ እንዳሉ መርምረና ከተቻለ በጸበልም ይሁን በዱአ ካላባረርን የተሳለ ህይወት አይኖረንም። እኛ የጭቆና መሳሪያዎች መሆን ካላቆምን ጭቆና ከዚህ ሀገር አይወጣም። እኛ እራሳችንን ሳናጸዳ፤ እራሳችንን ነጻ ሳናወጣ በሌላው በማመካኘት ለውጥም እድገትም አልመጣም።
ጨቋኝ ማነው፤ መንግስት የሚባል ምናባዊ ሰው ወይስ እኛ? የጭቆና መሳሪያዎች እኛ ነን። ስለዚህ ወታደር ከሆኑ ተኩሶ በመግደልና በመሳት መሀከል ያለው ህሊና ፍርድ እንጂ ታዝዤ ነው አትበል። ውሸታም ነህ። ፓሊስ ከሆንክ ሰው በመግረፍና በማጉላላትና የታሳሪን መብት በማክበር መሀከል ያለው ህሊና ነው። ሰው አሰቃይተህ ታዝዤ ነው አትበል። ነገም አንተን በተራ የሚገርድ ይቀጠራል። ሚሊሽያ፤ ልዩ ሃይል፤ ደንብ አስከባሪ፤ ዘበኛ፤ ትራፊክ፤ ገቢዎች፤ የመንግስት ንግድ ቢሮ፤ ኢሚግሬስን ሆነህ የህዝብን መብት እየገፈፍክ ተጨቆንኩ አትበል። እንደውም ይበልህ ነው የሚያስብለው። እራስህ ጨቋኝ ሆነህ መብት ይገባኛል አትበል። መጀመሪያ ከጨቋኝነት እራስህ አጽዳ።
ጨቋኜ ማነው ብለን መጠየቅ አለብን። እንደው ጉልቻ እያቀያየርን ወጡ እንዲጣፍጥ ብናስብ ያስ እህል ውሀ የማይል ስሮ ነው። በሚቀጥለው ስለ ጭቁና ስነልቦና እመለሳለሁ።
መደምደሚያ
አለመናገር፤ ፓለቲካ አልወድም ማለት አንደኛ ፈሪነት እንጂ ምክናታዊነት አይደለም። ሰው ሆኖ መብት አለኝ ብሎ የሚያምን ሁሉ ፓለቲከኛ ነው። ፓለቲካ ለመብት ለተሻለ አለም፤ ለተሻለ ህይወት ማሰብ እንጂ እግርኳስ ወይ አትሌቲክስ አይሰለም። የአንባገነን ስርአት ድጋፍ መስጠት ነው። የአሜሪካን ጥቁር መብት ተሟግቻ ማርቲን ሉተር ይሄንን ይላልው።“History will have to record that the greatest tragedy of this period of social transition was not the strident clamor of the bad people, but the appalling silence of the good people.” እንዲሁም “Our lives begin to end the day we become silent about things that matter.” ስለሲህ አለመናገር አዋቂነት ሳይሆን የስነ ልቦና ባርነት ነው።
ደግሞ
አንቶኒዮ ግራምቺ የሚባል የጣልያን ኮሚኒስት ለጭቁኑና ለሰራተኛው ለመታገል የኮሚኒስት ፓርቲ ፈጥሮ ይታገል ነበር። ያኔ ሞሶሎኒም ወጣት የሶሻሊስት ፓርቲ አባል ሆኖ እንደ አንቶኒዮ ግራምቺ ለጭቁኑና ለሰራተኛው መደብ ለመታገል የወሰነ ነበር።
ያሬድ ኃይለመስቀል
Yaredhm.yhm@gmail.com