
የፕሪቶሪያ ስምምነትና “የአወዛጋቢ መሬቶች” ጉዳይ
በአንበርብር ሀይሉ
የፕሪቶሪያ ስምምነት ትልቁ ችግር፣ የጉዳዩ ቀጥተኛ ባለቤቶች የሆኑትን አማራን፣ አፋርንና ኤርትራን በሴራ ማግለሉ ነው። ኦነግ ከአስመራ ወደ ኢትዮጵታ ሲገባ፣ ድርድሩ የነበረው በለማ መገርሳ በተመራው ኦህዴድና በኦነግ እንጂ፣ የፌዴራል መንግስት አልተወከለም ነበር። በድርድሩ ይዘት ላይ ያላቸውን ንትርክ ስናስተውል፣ እስከ አሁን ድረስ ምን እንደተስማሙ ከኦህዴድና ከኦነግ ውጪ ማንም የሚያውቅ የለም።
ዘመነ ትህነግ በማናቸውም መመዘኛ በሁሉም ነገር ብሄረ ኢትዮጵያኖችንና አማራውን በተንኮል ያገለለ፣ ህግ አውጥቶ የተበቀለ ስርዓት ነበር።
የሰኔ 24 የወያኔ የሽግግር መንግስት ምስረታ ኮንፈረንስ፣ የወያኔ ህገ መንግስት/ህገ ሕወሃት ሲረቀቅ፣ …..አማራው አልተወከለም ነበር።
አማራው በብአዴን ስም በኤርትራዊው በረከት ስምዖን ተወክሎ፣ የወልቃይት በጠራራ ፀሃይ መሰረቅ አልበቃ ብሎ፣ ተጨማሪ የጎንደር መሬት ለትግራይ ተቆርሶ ቢሰጥ ምን ችግር አለበት ብሎ ስብሰባ ላይ በድፍረት ካለምንም ይሉኝታ ተከራክሯል።
የደቡብ ተወላጅ የሆነው ታምራት ላይኔ ደግሞ፣ ወያኔ ስልጣን እንደያዘ በአማራ ስም አስመራ ድረስ ሄዶ ኤርትራ ውስጥ ለጠፋው ጥፋት ሁሉ ተጠያቂው አማራና አማራ ብቻ ስለሆነ፣ በአማራ ስም ይቅርታ ጠይቆ መጣ።
የአብይ ብልጽግና ደግሞ በፕሪቶሪያ ስምምነት አማራውን በማግለል ኢህአዴግ ቁጥር 2 ቁርጥ የአባቱ ልጅ መሆኑን በተግባር አሳይቷል።
በቅርቡ ሬድዋን ሁሴንና ጌታቸው ረዳ በፋና ቴሌቪዥን ቀርበው፣ የፕሪቶሪያን ስምምነት በአለቀ ሰዓት ሊደናቀፍ ነበር ሲሉ ተደመጡ። አደናቃፊው ጉዳይ ደግሞ “አወዛጋቢ መሬቶች” የሚባሉት እነ ወልቃይት የአማራው ቀይ መስመሮ ናቸው።
ሲጀምር አወዛጋቢ መሬት የሚባል የለም። በታሪክም፣ በህግም ወልቃይት የጎንደር፣ ራያ አላማጣ የወሎ መሬት ናቸው።
እነዚህ የአማራው ቀይ መስመሮች ወያኔ ገና ጫካ እያለ፣ የሕወኃት የፓርቲ ፕሮግራም እንዳለ ተቀድቶ ወደ ህገ መንግስት/ህገ ህወሃት ከመቀየሩ በፊት፣ የሽግግር መንግስት ከመመስረቱ በፊት፣ በኃይል በማን አለብኝነት ከጎንደርና ከወሎ በስርቆት የተወሰዱ መሬቶች መሆናቸው ማንም ያውቀዋል።
የወያኔ ተረት ተረት ዋና ፈብራኪ ስብሃት ነጋም ፣ ከትግራይ ጦርነት በፊት በአንድ ወቅት ጋዜጠኛ ዳዊት ከበደ የበላይ ሆነን መኖር ካልቻልን መገንጠል አይሻለንም ወይ ብሎ ስብሃት ነጋን ሲጠይቀው፣ የስብሃት ነጋ አንዱ መልስ ወልቃይትን ይዘህ ልገንጠል ብትል አማራው ይለቅሃል ወይ ነበር። ወልቃይት የጎንደር እንደሆነ እነሱም ብዥታ እንደሌለባቸው ጥሩ ማሳያ ነው።
አማራ፣ አፋርና ኤርትራ በቀጥታ የጦርነቱ ተሳታፊዎች እንደመሆናቸው መጠን፣ ለዘለቄታ ሰላም ሲባል በፕሪቶሪያ ስምምነት የግድ መካተት ነበረባቸው። ደመቀ መኮንን የተደራዳሪዎች መሪ ይሆናል ተብሎ፣ በድንገት በሬድዋን ሁሴን በአብይ ተተክቷል። የኦሮሙማ አራማጆች ተንኮል እንዳለበት ግልጽ ነው።
ነገር ግን ዶ/ር ጌታቸው በወቅቱ የአማራ ክልል ም/ፕሬዜዳንት ደግሞ በታዛቢነት መገኘቱ፣ የወልቃይትን ጉዳይ ሬድዋንና ጌታቸው አደባብሰው ሊያልፉ ሲሞክሩ፣ በማንሳቱ ነበር ባለቀ ሰዓት ድርድሩን ሊያደናቅፍብን ነበር ያሉት።
ሬድዋን ሁሴን የወያኔ ስርዓት ከተቋቋመ ጀምሮ፣ የብሄር ፓለቲካን ሲያቀነቅን የነበረ የስልጤ ተወካይ ነው። ወልቃይት ለሬድዋን “የስልጤ መሬት” ስላልሆነ፣ ምናልባትም እንደ ማናቸውም ጎሰኞች ሊኖርበት ከሚችለው ጭፍን የአማራ ጥላቻ እነ ወልቃይትን በወያኔ እጅ ቢገቡ ሊመርጥ ይችላል።
የፕሪቶርያው ስምምነት ላይ ዶ/ር ጌታቸው የእነ ወልቃይትን ጉዳይን ባለቀ ሰዓት ማንሳቱ ያልተመቻቸው አማራ ጠሎች፣ በቀጣዩ የናይሮቢ ድርድር ላይ አማራዎችን ከታዛቢነት ሳይቀር ሙሉ ለሙሉ አስወግደው፣ በስልጤው ሬድዋን ሁሴንና በኦሮሞው ብርሃኑ ጁላ ከትግራይ ጎሰኞች ጋር በጎንደርና በወሎ መሬቶች ጉዳይ እንዲደራደሩ ተደረገ።
የናይሮቢ ድርድር ዋና አላማው የፕሪቶሪያ ስምምነት ዝርዝር ማስፈጸሚያ ሰነድ ማርቀቅ ቢሆንም፣ በናይሮቢ ስምምነት ዋናውን የፕሪቶሪያን ስምምነቱን የሚጻረር ውሳኔዎች ሬድዋን፣ ጁላ፣ ጌታቸው ራዳና ጻድቃን ፈጸሙ።
የፕሪቶሪያው ስምምነት በማያሻማ ቋንቋ ወያኔ በሳምንታቶች ውስጥ ሙሉ ለሙሉ ትጥቅ ይፈታል ሲል፣ በናይሮቢ ድርድር ላይ አማራውን አግለው ወያኔ ከአካባቢው ያለበትን የደህንነት ችግር ባገናዘበ መልኩ ትጥቅ እጁ ላይ እንዲቀር ይደረጋል ብለው እነ ሬድዋን ተፈራረሙ። በፕሪቶሪያ ስምምነት መሰረት ወያኔን ሙሉ ለሙሉ ትጥቅ ማስፈታት ሲገባቸው፣ የመከላከያ የአደጋ ጊዜ ተጠሪ የነበረውን የአማራን ልዩ ኃይል ትጥቅ እናስፈታለን ብለው፣ የኦሮሙማ አራማጆች የፋኖ ትጥቅ ትግል እንዲጀምር አንዱ ዋናው ምክንያት ሆኑ።
በፕሪቶሪያ ስምምነት ላይ የውጭ ኃይሎች ከትግራይ ይወጣሉ ሲል፣ ናይሮቢ ላይ ግን እነ ሬድዋን ከፌዴራል ታጣቂዎች ውጪ ታጣቂዎች ከትግራይ ይወጣሉ በሚል ተስማሙ። የፕሪቶሪያው ስምምነት አወዛጋቢ ቦታዎች ባሉበት ይቆያሉ ሲል፣ የኖይሮቢው ድርድር ደግሞ ጉዳዩን አድበስብሶት አለፈው።
የናይሮቢ ድርድር የፕሪቶሪያ ስምምነት ዝርዝር ማስፈጸሚያ ሰነድ እንደመሆኑ፣ ዋናውን የፕሪቶሪያን ስምምነት የሚጻረር በናይሮቢ ድርድር የተጨመረ ማናቸውም አንቀጽ በህግ ተቀባይነት አይኖረውም።
ስለዚህ በፕሪቶሪያ ስምምነት መሰረት፣ ወያኔ ሙሉ ለሙሉ ትጥቅ መፍታት አለበት፣ ትግራይ ውስጥ የፌዴራል መንግስትን ጨምሮ የተለያዩ ኃይሎች የተወከሉቡት ጊዝያዊ አስተዳደር መመስረት አለበት እንጂ፣ ለወያኔ ብቻ መተው አልነበረበትም። የዘለቄታ መፍትሄ እስኪመጣ ድረስ፣ የገንደርና የወሎ ርስቶች ወልቃይና ራያ አላማጣ በፕሪቶሪያ ስምምነት መሰረት ባሉበት በአማራው እጅ መተዳደር አለባቸው። ስልጤው ሬድዋን፣ ኦሮሞው ብርሃኑ ጁላ፣ ከወያኔ ትግሬዎች ጋር አማራን ወክለው በአማራው በጎንደርና በወሎ መሬት ጉዳይ በፍጹም መደራደር አይችሉም። ስምምነታቸውም ተቀባይነት አይኖረውም።