የአዲስ አበባ ቆይታዬና ትዝብቴ (ክፍል 2)

የአዲስ አበባ ቆይታዬና ትዝብቴ (ክፍል ሁለት)

በፍሬው አበበ

ከክፍል 1 የቀጠለ

2. ስንቄ ባንክ

“በሸገር” ከተማ የሚከፈለው ግብር በሙሉ የሚገባው ስንቄ ባንክ ነው። በባንኮች መካከል ፉክክር የለም። ለተገልጋዩ አማራጭ አይሰጥም። በግዴታ ወደ ባለጊዜው ስንቄ ባንክ የግድ መከፈል አለበት።

በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ቁልፍ ቁልፍ ቦታዎች ላይ አዳዲስ ህንጻዎች ውስጥ ጨምሮ የሚከፈተቱት አብዛኛው አዳዲስ የባንክ ቅርንጫፎች የገዢው የኦህዴድ ባንኮች (ስንቄ፣ ኦሮሚያ ባንክ፣…) ናቸው። እንዴት? ለምን?

3. የኦህዴድ ባንኮች አዲስ አበባ ውስጥ ስያሜ

አዲስ አበባ ውስጥ ያሉ የኦህዴድ ኦሮሞ ባንኮች ስያሜዎች ከአዲስ አበባ ህዝብ ስነልቦና ጋር የማይሄዱ፣ ስሞቹ በሙሉ ከአዲስ አበባ ታሪክና ሰፈሮች ጋር አንዳችም ግኑኝነት የሌላቸው፣ የማይታወቁ ባዕድ ስሞች ናቸው። ለምሳሌ ሌሎች ባንኮች አዋሽ ባንክን ጨምሮ ፒያሳ አካባቢ ቅርንጫፍ ቢከፍቱ፣ የእከሌ ባንክ የፒያሳ ቅርንጫፍ ይሉታል።

በዚህ የኦህዴድ ባንኮች የአዲስ አበባ ጠል አሰራር፣ የቅርንጫፎቹ ስሞች በሙሉ ለአዲስ አበቤዎች ባዕድ ናቸው። ኦህዴድ ከስልጣን ሲወገድ አትራፊ ተፎካካሪ ሆነው አዲስ አበባ ውስጥ መቀጠል ይከብዳቸዋል።

4. የሚሊሽያ ክፍያ

“በሸገር” ከተማ ህግ የማያቀው የሚሊሺያ ክፍያ በሚል ነዋሪው ላይ የተጣለው ቀረጥ የሚሰበሰበው ብር ደረሰኝ የለውም። የሚገባውም የግለሰብ ባንክ አካውንት ውስጥ ነው። በግለሰብ አካውንት ውስጥ ማስተላለፍ ህጋዊ አሰራር ስላልሆነ፣ በድፍረት አንከፍልም ብለው እስከአሁን የማይከፍሉ ብዙ ሰዎች እንዳሉ ተረድቼያለሁ።

5. የሁለት የሸገር ልጆች ራይድ ሹፌሮች ወግ

ሁለት የራይድ ሹፌሮች በተለያየ ጊዜ ያወጉኝን ላካፍላችሁ። ሁለቱም የአዲስ አበባ ልጆች ናቸው። ሁለቱም በእናታቸውም በአባታቸውም የኦሮሞ ተወላጅ እንደሆኑ አጫውተውኛል።

አንደኛው ሹፌር ከፒያሳ ወደ ቦሌ ስንሄድ፣ መስቀል አደባባይ ልንደርስ ስንል ትራፊክ ፓሊስ ቆሞ ያያል። ፊቱ ሁሉ ተለዋውጦ ይኸውልህ እንዚህን አብይ አምጥቶ አፈሰሰብን አለ። ስላልገባኝ እነማንን ስለው፣ የአብይ ካድሬ ይሆናል ብሎ ገምቶኝ መሰለኝ ትንሽ ድንገጥ አለ። ቀጠል አድርጎ እኔ በእናቴም በአባቴም ኦሮሞ የሆንኩኝ አዲስ አበባ ልጅ ነኝ። ስለዚህ የኦሮሞ ጥላቻ ሊኖረኝ አይችልም።

ነገር ግን ትራፊክ ፓሊሶቹ በሙሉ ከኦሮሞ አካባቢ ነው ያመጧቸው። አማርኛ ቋንቋ በደንብ አይችሉም፣ ስራውን በደንብ አያቁም፣ በዚህ ላይ ለአዲስ አበባ ሰው ትልቅ ጥላቻ አለባቸው። ከእነሱ ጋር ጭቅጭቅ ነው። ስራ አላሰራ እያሉ በጉቦ አስቸግረውናል አለ።

ሁለተኛው የራይድ ሹፌር ደግሞ የተሳፈርኩት ከሳርቤት ወደ መርካቶ ነበር። አዲስ በኤሌክትሪክ የሚሰራ መኪና ስለያዘ፣ አዲስ ሹፌር ነህ ብዬ ስጠይቀው፣ አዎን የግል ስራችንን አብይ ከመጣ በኋላ አላሰራ ብሎን፣ የሰፈሬ ልጆች በሙሉ ሲሰደዱ፣ ቤተሰብ ስላለኝ ከመሰደድ ራይድ ጀመርኩ አለ።

አብይ ያፈናቀለኝ ከስራዬ ብቻ ሳይሆን፣ ስንት ውጣ ውረድ አይቼ የሰራሁትንም ቤት ህገ ወጥ ብሎ አፍርሶብኛል ብሎ ጨመረበት ።

እኔና ቤተሰቦቼ ሙሉ ለሙሉ ኦሮሞ ብንሆንም፣ የኦሮሞ ስም ስለሌለንና ኦሮምኛ ስለማንናገር፣ “አማራ” ብለው ፈርጀውን ቤታችንን አፍርሰው “ከሸገር” አፈናቀሉን። በጣም የሚገርመው ጎረቤቴ የእህቴ ባል በብሄሩ ሙሉ አማራ የሆነ፣ ኦሮምኛ ስለሚችል ብቻ በኦሮምኛ አናግሯቸው እንደ ኦሮሞ ወስደውት ቤቱ ከመፍረስ ዳነ። ይህቺ ናት የአብይ ኢትዮጵያ። ወያኔን ተገላገልን ስንል የባሰው መጣና አረፈው። እግዜር ይሄን ዘረኛ መንግስት መጨረሻውን ሳያሳየኝ አይግደለኝ አለ።

6. ሱሉልታ

ሱሉልታ ከተማ ውስጥ ደግሞ ታክስ በግዳጅ የሚከፈለው ለኦሮሚያ ባንክ ብቻ ነው። ሱሉልታም በባንኮች መካከል ምርጫ፣ ውድድር የሚባል ነገር የለም።

ከተማው እየተዳከመ መጥቷል። ማለቂያ በሌላቸው ህገ ወጥ መዋጮና በጉቦ ነጋዴው ተማሯል። ዘረኝነቱ አይን ያወጣ ነው። በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንዲሉ፣ ስራም በጣም እየቀዘቀዘ ስለመጣ፣ ብዙ ባለሃብቶች ሱሉልታን እየለቀቁ እየወጡ ነው። የቀረውም ለመውጣት ዳር ዳር እያለ እንደሆነ ለብዙ ዓመታት በሱሉልታ ነጋዴ የሆኑ ሰዎች አጫውቶውኛል።

7. አዋሽ ባንክ

ኢትዮጵያ ውስጥ አንዳንድ ባንኮች በጎሳ እንደታዋቀሩ ለመጀመርያ ጊዜ ያወቅኩት፣ በግማሽ የኦሮሞ ተወላጅ የሆነ በጊዜው ለኦነግ የሚሰራ አብረን የተማርን ቢራ ላይ ስለ አዋሽ ባንክ ባጫወተኝ ጊዜ ነው።

ኦሮሞ ካልሆንክ አዋሽ ባንክ አትቀጠርም አለኝ። መጀመርያ የሚቀልድ መስሎኝ ነበር። በኋላ ግን ረጋ ብሎ በምሳሌ አብራራልኝ።

ወደ ቅርቡ ጉዞዬ ትዝብት ስመለስ፣ አንድ አዲስ አበባ ውስጥ ባለ የአዎሽ ባንክ ቅርንጫፍ የተፈጠረው ጉዳይ ከልክ ያለፈ ኩነት ላውጋችሁ። ትውልዷና እድገቷ አዲስ አበባ የሆነ አንዲት ፕሮፌሽናል ሴት፣ ብር ልታወጣ ወደ አዋሽ ባንክ ትሄዳለች። ልጅቷ ኦሮሞ ናት። የባንክ ደብተሩ ላይ ያለው ስሟም የማያሻማ የኦሮሞ ስም ነው።

ባንክ ሰራተኛው የባንክ ደብተሯ ላይ ያለውን ስሟን አይቶ፣ በኦሮምኛ ማናገር ይጀምራል። ልጅቷ ኦሮምኛ ስለማትችል፣ ምን እያልክ ነው ብላ በትህትና ትጠይቀዋለች። ኦሮሞ ነሽ ብሎ ይጠይቃታል፣ አዎን ብላ ትመልሳለች። ኦሮምኛ ትችያለሽ ብሎ ይጠይቃታል፣ አልችልም ብላ ትመልሳለች።

ባትፈጠሪ ይሻላል ብሎ እንባረቀባት። የባንክ ደምበኛህን በማያገባህ ገብተህ እንዲህ ከፍ ዝቅ አድርገህ የምትሰደብ ዘረኛ ከብት ነህ ብላ በቁጣ ተናገረችው። የባንክ ደብተሯን እዛው ቀዳው፣ የባንክ ማኔጀሩን አስጠርታ ቅሬታዋን ገልጻ ወጣች። የባንክ ማኔጀሩ ልጅቷን አረጋግቶ ይቅርታ ጠይቆ እንደወጣች አጫወተኝ።

የኦህዴድ የዘረኝነትና የተረኝነት ቫይረስ ተሸካሚዎች እንዲህ አይን ያወጣ ወራዳ የማያቀባብር ስራ ውስጥ ነው የተጠመዱት።

ክፍል ሶስት ይቀጥላል..

 

Related:
የአዲስ አበባ ቆይታዬና ትዝብቴ (ክፍል-1)

guest

0 Comments
Oldest
Newest Most Voted
Inline Feedbacks
View all comments

0
Would love your thoughts, please comment.x
()
x