ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች የሚለው የመለስ ፈጠራ ምንጩ ማነው?
በያሬድ ኃይለመስቀል
ብሔር ብሔረሰብና ህዝቦች የሚለው ቃል ትልቁ የማይደፈር እና የሚፈራ ጣኦት ሆኖ ለ34 ዓመት ገዝቷል። ይሄንን ቃል መተቸት የሚያሰገድል የሚያስገርፍ የሚያሳስር ነበር። እሱ የብሔር ብሔረሰቦች ጠላት ነው የሚለውን ክስ ሁሉን ብርክ የሚያስይዝ ቃል ነበር።
በመንግስቱ ግዜ ጸረ-አብዮተኛ፣ አናርኪስት፣ ፊውዳል ከባሚለው ክስ በላይ የሚያስፈራ ነበር። እነኚህ ጸረ ስርአትና መንግስት ስያሜዎች ናቸው። ጸረ ብሔር፣ ብሔረሰቦች ማለት ግን የህዝብ ንቀት ተብሎ የሚያስከስስና ምህረት የሌለው ወንጀል ነበር።
ታድያ እነዚህን ቃሎች መለስ ከየት ተዋሳቸው። ለምን በማርክሲስዝምም በስታሊንም ጽሁፍ ውስጥ አናገኛቸውም የሚለውን ጥያቄ ያነሳ ወይንም የተረጎመ የለም።
ጥያቄ – ብሔር_ብሔረሰቦችና_ህዝቦች ማለት ምንድነው? ከየት መጣ? ለምን ማሀበረሰቦች ተበላልጠው በሶስት ደረጃ ተመደቡ?
ብሔር – ዐምሓራ፣ ኦሮሞ እና ትግሬ ሲሆኑ፣ ከብሔረሰቦች ማለትም ሲዳማ፣ ሀድያ፣ ጉራጌ በምን መመዘኛ ከዐምሓራ፣ ኦሮሞና ትግሬ ያንሳሉ? በምን መመዘኛ? በባህል፣ በደም፣ ባጥንት፣
ለምን እነ ኮንሶ፣ ቱርሚ ወዘተ በህዝቦች ተብለው ተመደቡ። ለምን የነሱ ባህል፣ ቋንቋ ከኦሮሞ፣ከትግሬ ያንሳል የሚል ድምዳሜ ላይ ተደርሶ በሶስተኛ ሊግ ይጫወቱ ተባለ?
እኩል ናቸው ብለን ካሰብን ለምን ሁሉም #ብሔር ተብለው አልተመደቡም።
ለምን ለሶስቱ ፕሪሚዬም ሊግ፣ ለ54 ደግሞ ሶስተኛ ዲቪዚዎም መፍጠር አስፈለገ?
ኤሪክ ሆፈር (Eric Hoffer) የሚባለው ፈላስፋ “ሰዎች እንደ ፍጹም እምነት አድርገው የሚቀበሉት ያልገባቸውን ጽንሰ ሀሳብ ነው ይላል። ስለዚህ አንድን ጽሁፍ ወይም ዶክትሪን ሰዎች እንዲያምኑት እንዲያመልኩት ከፈለክ በጭራሽ እንዳይረዱት አድርገህ ጻፈው ይላል። የገባችው ቀን ከነሱ እንደመነጨ ያስቡና ይንቁታል ይላል”።
ኢትዮጵያ ውስጥ መለስ የተጫወታት በኛ ግዜ አራዶች ቋንቋ “ፊንታ” ይቺ ናት።
ስለዚህ የመለስ ቃላትን ድርደራ ግራ ማጋባት የተካነበት ነው፣ ብሔር-ብሔረሰቦች፣ ቦና_አፐርቲዝም፣ አንዮታዊ_ዲሞክራሲ ወዘተ ብሎ ቃል ይጥላል። እነ ሰዬ ቦናፐርቲዝም ሲል መልካም እራት ማለቱ ይሆን ብለው ጸገራቸውን እያሻሹ ሲያሰላስሉ ቃሊቲ እራሳቸውን አገኙት።
ሌላው ይህ ማሰብ፣ ማንበብ፣ መጠየቅ፣ የማይችለውን መንጋና ካድሬ ህዝብ ተከታይ አድርጎ ለመጋለብ በደንብ ተጠቅሞበታል። በደንብም ሰርቷል። ታጋይ መለስን ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ምን ማለት ነው? በምን ይበላለጣሉ? ብሎ የጠየቀው አንድ ሰው የለም።
እንደውም ስድቡን እንደ በጎ ቆጥሮ እኛ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ከጠቅላይ ሚኒስቴር መለስ ጋር ወደፊት አሉ። ሰው በመሰደቡ ሲኩራራ፣ ለስድቡ እሞታለሁ ሲል ታየ። የሚቀጥለው የብሔር ብሔረሰቦች ልጆች በአባቶቻቸው ድንቁርና ያዝናሉ።
ጀነራል ምግበ በመጨረሻው ሲናደድ ብልጭ ሲልበት እንደሰማነው “ልብስ አልብሰናቸው ተነሱብን” ያለው ብሔሮችና ህዝቦች የኛ ብሔር ላደረገላቸው ውለታ ቢስ ሆኑ ለማለት ነው።
ታድያ የብሔር ብሔረሰብና ህዝቦች ቃልና ጽንሰ ሀሳብ ከየት መጣ? አቶ መለስስ ከየት አገኘው? በአንድም በማርክሲስት ሆነ ስታሊን ጽሁፍ ውስጥ ለምን ይህ ፍረጃና ማበላለጥ አልተጻፈም ብለን መጠየቅ ሰአቱ ነው።
ምንጩ #Primitive_Culture ከሚለው የእንግሊዝ ዘረኛ አንትሮፓሎጂስት ነው። ኤድዋርድ ቴለር ዳርዊን የዝግመተ ለውጥን ሀተታ ካሳተመ ቦሀላ ይህ ዝግመተ ለውጥ ህግ ለባህልም ይሰራል ብሎ ስለ #ሗላ_ቀር ባህሎች Primitive Culture የሚለውን መጽሀፍ በ1871 አሳተመ። በዚህ መጽሀፍ ውስጥ የባህልን ዝግመተ ለውጥ በሶስት ከፈለው። ፩ኛ Savages ( አረመኔ ህዝቦች)፣ ፪ኛ Barbarians ( ያልሰለጠኑ – ብሔረሰቦች) እና Nations/ Civilized ስልጡን -ብሔር ብሎ መደበ።
በዚህ ውስጥ እንግሊዙ ጀርመኑ ሲዊድኑ ሲንፎኒ ኦርኬስትራ ያለው፣ ኦፕራ የሚያዳምጠው፣ በሹካ የሚበላ፣ ጽሁፍና ምናባዊ እይታ ያለው የሰለጠነው ብሔር ሆነ። ማለትም በዝግመተ ለውጥ ከዝንጀሮ ፈጥኖ ነጭ፣ ባለ ወርቃማ ጸጉሩና ሰማያዊ ቀለም አይን ያለው ሰው Nation ስልጡን ብሔር ብሎ መደበው።
ከዛ ይህ ጥቁር ጸጉር ያለው፣ አርሶ የሚበላውን የምስራቅ አውሮፓ ህዝብን ከባርባርያንስ ማለትም ጨካኝ ያልሰለጠኑ አላቸው።
ሶስተኞቹ አፍሪካውን እና ሌላውን በአጠቃላይ በዝቅተኛው የሰው ልጅ ዝግመተ እድገት በመጀመሪያው መሰላል ላይ አሉ ያላቸውን Savage/አረመኔ ብሎ ሰየማቸው። ጽሁፍ፣ ምናባዊ እሳቤ የሌለው ( abstract knowledge ማለትም እንደ ሂሳብ ፍልስፍና ያለውን ነገር አይምሮው መቀበል የማይችል) ብሎ መደባችሁ። በሹካ ሳይሆን በእጃችሁ የሚበሉ በዛ መደባችሁ:-)
Edward Burnett Tylor’s Primitive Culture (1871) is a foundational text in anthropology, introducing the first formal definition of culture and proposing a theory of cultural evolution from “savagery” to “civilization….societies progress through stages: savagery → barbarism → civilization. ማለትም ከጌዲዮ ወደ ሲዳማ ከዛ ወደ ኦሮሞነት፣ አምሓራነት፣ ትግሬነት የሚደረግ ዝግመተ ለውጥ ማለት ነው።
መለስ ሲዳማን ከትግሬ እኩል አድርጎ ለመመደብ እድገቱ እና ትምክህቱ አይፈቅድለትም። ወርቅና ጨርቅ አብሮ የማይቆም ነውና አልፈለገም።
እንግዲህ መለስ የአድዋ ልጅ ቢሆንም ጀነራል ውንጌት መጥቶ በአራዳነት ተመርቋል። ስለዚህ ይሄንን ምንም ትርጉም የማይሰጥና የኢትዮጵያ ህዝብ በደረጄ ላይ አበላልጦ የሚመድበውን ዘረኛ Anthropology አምጥቶ ጫነው።
ኡስቂኙ ከዛ ብሔርብሔረሰቦች ወኪሎች ነን ያሉ ስለማያነቡ፣ ስለማይጠይቁ፣ ለምን ስለማይሉ ኮንሶ ከሲዳማ ያንሳል፣ ሲዳማ ከኦሮሞ ያንሳል የሚለውን ምደባ እንደ በጎ ተቀብለው የብሔር ብሔረሰቦች በደስታ በአቶ መለስ ፊት የብሔር ብሔረሰቦች ቀን ትርኢትና ዳንስ ማሳየት ገቡ። ሰው ያልገባውን ነገር ነው የሚያምነው ያለው ኤሪክ ሆፈር ይሄንን ነው።
ስለዚህ ከዚህ የምንማረው ሰዎች እሞትለታለሁ የሚሉት፣ እንገልለታለን እንሞትለታለን የሚሉለት ጽሁፍ ዶክትሪን ካለ እነዚህ ሰዎች ምን ጽንሰ ሀሳቡ አልገባቸውም ማለት ነው።
አረመኔ፣ ጨልካኝ ሳቬጅና ባርባርያንስ ተብሎ መመደብ ደስ የሚያስብል ስም በኢትዮጵያ ውስጥ የሆነበት ምክንያት የሚያምኑ እንጂ የማይጠይቁ ሰዎች ስለበዙ ነው።
ከዚህ የምንማረው ምን ማለት ነው ብሎ መጠየቅ ያስፈልጋል። ሳይጡይቁ መከተለ ምናልባትም አንዳንድ ሰዎች በእርግጥ ዝግመተ ለውጡ ውስጥ አልገቡ ይሆን እንዴ ያስብላል።
ኤድዋርድ ቴይለር እውነት ይሆን እንዴ ያስብላል? በእርግጥ ምናባዊ እውቀት (abstract knowledge) መቀበል የማይችል አይምሮ ያላቸው ፍጡራን በኢትዮጵያ ይኖሩ ይሆን እንዴ ያስብላል፣ ያስገምታል።
ኤድዋርድ ቴይለር የኦክስፎርድ ፕሮፌሰር ሲሆን የነ አሰፋ ጃለታ አንትሮፓሎጂና ሶስዎሎጂ አባት የሚሉት ሰው ነው። እንግዲህ ሳቬጅ ለሚለው ስያሚያችሁ ፈጣሪ እሱ ነው።