አዲስ አበባ በ170ዎቹ
አዲስ አበባ በ170ዎቹ

አዲስ አበቤነት!

በፍሬው አበበ

“አዲስ አበባ ቤቴ” የሚል ግጥም በገጣሚ ምልዕቲ ኪሮስና የመቅደስ ገ/መድህን (የለታይ ልጅ) የተለያዩ ግጥሞች ትናንት ማምሻዬን አዳመጥኩኝ። ግጥሞቹ ለመድረክ ከቀረቡ ትንሽ ቢቆዩም፣ ስሜቴን በእጅጉ ስለኮረኮሩት ይሄን መጣጥፍ ለመጻፍ ወሰንኩኝ።

“የአዲስ አበባ ቤቴ” ገጣሚ ምልዕቲ ኪሮስ የጨርቆስ ልጅ፣ መቅደስ ገ/መድህን (የለታይ ልጅ) ደግሞ የተክልዬ ልጅ ናት። ከስማቸው ሁለቱም ቤተሰቦቻቸው ትግርኛ ተናጋሪዎች መሆናቸውን መገመት ይቻላል።

የምልዕቲ ግጥም የተገጠመው ለእነ ጃዋርና ለእነ ዶ/ር ዘላለም ሙለታ ለመሳሰሉት ህገወጦች፣ ጠባብ ጎጠኞችና ባለጊዜዎች መልስ እንዲሆን ታስቦ ይመስላል።

በመጀመርያ እምነቴን በአጭር ቋንቋ ግልጽ ላድርግ። የተለያዩ ጎሳዎች የሚያዳብሩትና የሚንከባከቡት ቋንቋ፣ ባህል፣ ወግ፣ ትውፊት፣….አላቸው። ሁሉም ብሄሮች በቋንቋቸው የመማር፣ የመዳኘት፣…የማይሸራረፍ መብታቸው ህጋዊ ጥበቃ ሊደረግላቸው ይገባል።

የመሬት ባለቤትነት ላይ ስንመጣ ግን፣ የኢትዮጵያ መሬት እንጂ የብሄር መሬት የሚባል የለም። በምሳሌ ለማብራራት የአማራ፣ የጉራጌ፣ የአፋር፣….ቋንቋ፣ ባህል፣ ወግ፣….አለ። የሱማሌ፣ የትግሬ፣ የኦሮሞ፣…. መሬት የሚባል ግን የለም።

እዚ ላይ ልብ ማለት ያለብን ነገር ቢኖር፤ የአማራ፣ የኦሮሞ፣ የትግሬ፣ …..መሬት የሚባል የለም ስል፣ የወሎ፣ የወለጋ፣ የሸዋ፣ የትግራይ፣… መሬት ግን የለም ማለት አይደለም።

በኢትዮጵያ ታሪክ የጠቅላይ ግዛት/ ክፍለ ሀገር መሬት ከጂኦግራፊ ጋር የተዛመደ እንጂ፣ ከእንድ ጎሳ ጋር አይገናኝም። ክፍለ ሀገሮች የብዙ ሺህ ዘመን ታሪካዊ መሰረት ያላቸው በቀላሉ ማንም ሊያጠፋቸው የማይችል መሆናቸውን የዘመኑ ኋላ ቀር የጎሳ ፓለቲካ አራማጆች ሊያውቁት ይገባል።

ወሎ ጠ/ግዛት ውስጥ አማራ፣ አገው፣ ኦሮሞ፣ አፋር፣ አርጎባ፣….ይኖራል። ሸዋ ውስጥ አማራ፣ ኦሮሞ፣ ጉራጌ፣ ከምባታ፣ ሃዲያ፣…ይኖራል። ትግራይ ውስጥ ትግሬ፣ አገው፣ ኩናማ፣ ይሮብ፣ ሳሆ፣ አፋር፣….ይኖራል። ጅማ ውስጥ ኦሮሞ፣ አማራ፣ ከፋ፣ ጃንጀሮ፣….ይኖራል።

ይሄ ማለት የወሎ፣ የወለጋ፣ የአርሲ፣ የሀረርጌ፣….መሬት አለ። ነገር ግን አንድ ክፍለ ሀገር የአንድ ጎሳ ሊሆን አይችልም። በአንድ ክፍለ ሀገር ውስጥ አንዱ ብሄር ከሌሎች ብሄሮች ሲነፃፀር በብዛት ሊኖር ይችላል። ለምሳሌ አማራ በወሎ ኦሮሞ ደግሞ በወለጋ ከሌሎች ጎሳዎች በንጽጽር በብዛት ይኖራሉ፣ ነገር ግን ወሎ የአማራ ወለጋ ደግሞ የኦሮሞ መሬት ነው ማለት ትክክል አይደለም።

መሬት ከጫፍ እስከ ጫፍ የሁሉም ኢትዮጵያዊ ነው ስል ግን የጆግራፊያዊ ስሜት የለም ለማለት አይደለም። የአዲስ አበባ ልጅ፣ የናዝሬት ልጅ፣ የድሬ ልጅ፣ የጎጃም ልጅ፣ የባሌ ልጅ፣ የሲዳሞ ልጅ፣..ስሜት አለ። ሊኖርም ይገባል። ተፈጥሯዊ ነው።

መሬት የኢትዮጵያ መሆኑ እንደተጠበቀ፣ የቅርብ ባለቤትነት ስሜት ከመጣ ግን የወለጋ መሬት ለወለጋ ልጅ እንጂ፣ ከወለጋ ልጅ ይልቅ ለአርሲ ልጅ አይቀርብም።

ጃዋር እምቡር እምቡር በሚልበት ዘመን፣ ጃል መሮ ከቢቢሲ አማርኛ ጋር ባደረገው ቃለ መጠይቅ፣ ጃዋር ስለ አርሲ እንጂ ስለ ወለጋ ከእኔ በላይ ምን አገባው ያለውም ለዚህ ይመስለኛል። በተጨማሪ ጃል መሮ ወለጋን ከኦሮሞ ባንቱስታን ክልል አውጥተን እራሱን የቻለ የፌዴራል ግዛት እንድትሆን እንሰራለን ብሏል።

አዲስ አበባም እንደ ኢትዮጵያ አካልነቷ፣ የሁሉም ኢትዮጵያዊ እኩል ርስት ናት። አዲስ አበባ ልክ እንደ ባህር ዳር፣ ጅማ፣ ድሬ፣ አሰላ፣ መቀሌ፣….የሁሉም ኢትዮጵያዊ ርስት ናት። እዚህ ላይ ምንም ብዥታ ሊኖር አይገባም።

ነገር ግን የቅርበት የቅርበት ጉዳይ ከተነሳ፤ ወለጋ ለወለጌው ጃል መሮ ከአርሲው ጃዋር በላይ ይቀርባል። የድሬ ልጆች ለድሬ፣ የሃዋሳ ልጆች ለሃዋሳ፣ የናዝሬት ልጆች ለናዝሬት፣… እንደሚቀርቡት ከአዲስ አበቤዎች በላይ ማንም ለአዲስ አበባ ሊቀርብ አይችልም። ማንም ከሸገር ልጆች በላይ የአዲስ አበባ ባለቤትነት ሊሰማው አይችልም።

አዲስ አበቤነት ደግሞ የግድ አዲስ አበባ ውስጥ ተወልዶ ማደግን መጠየቅ የለበትም። አዲስ አበባ ውስጥ የሚኖር የአዲስ አበቤነት ስሜት የሚሰማውና የአዱ ገነት ስነ ልቦና የተላበሰ ማናቸውም ሰው አዲስ አበቤ ነው።

ጃዋር ጤነኛ አይምሮ እስካለው ድረስ ከአርሲ መጥቶ ከአዲስ አበባ ልጆች በላይ የአዲስ አበባ ባለቤትነት ሊሰማው በፍጹም አይገባም። በምን ህግ፣ በምን አምክንዮ ነው የአዲስ አበባ ህዝብ ቆጥቦ የገነባውን የኮዬ ፈቼ ኮንዶምኒየም፣ የእርሲው ጃዋር ከህግ ውጪ በር ሰብሮ ለጎሳ አባሎቹ የሚያድለው? ከለማጋነን ትልቅ ድንቁርና፣ ትልቅ ድፍረት፣ ድልብ ስግጥና ነው።

ምልዕቲ በግጥሟ ላይ መሃል አገር የምንኖር፣ መሃል ግን ማን አድርሶን … ጊዜ የሰጠው ዘመናይ እንዳሻው የሚፈነጭብን፣… ከኢትዮጵያዊነት አንዲት ጋት ዝቅ የማንል፣…. ማነህ ምንድነህ ስንባል የራሳችንን የማንሰጥ የሰው የማንፈልግ የፒያሳ፣ የአራት ኪሎ፣ የፈረንሳይ፣ የጨርቆስ ልጅ የምንል፣…….. ስትል ትደመጣለች።

ምልዕቲ ለአዲስ አበባ የአርሲው ልጅ ጃዋር ከእሷ ከሸገር ልጅ በላይ እንደማይቀርብ፣ የራሴን የማልሰጥ የሰው የማልነካ ብላ ገጥማለች። ይሄ የአዱ ገነት ልጆች ሁሉ ስሜት ነው።

“ጊዜ የሰጠው ዘመናይ የሚፈነጭብን” ደግሞ “ከርሱን ሞልቶ ፈርሱን የሚጥል” ብሎ ያውም በፓርላማ ድፍን የአዲስ አበባን ህዝብ ለዘለፈው ለኦህዴዱ ዶ/ር ዘላለም ሙለታ የአዲስ አበባ የት/ቢሮ ኃላፊ የተሰጠ ምላሽ ነው።

የተክልዬዋ ልጅ መቅደስ ገ/መድህን ደግሞ የጎሳ ፓለቲካ ተጠይፋ፣ እርስ በእርስ በጎሳ ስትቧደኑ እኔ የለሁበትም፤ ኢትዮጵያን ሊያጠቃ ጠላት ሲመጣ ግን ያኔ ጥሩኝ፣ በእርስ በእርስ ጦርነት አያገባኝም ጎራ አልይዝም ብላለች።

ጋዜጠኛ አርአያ ስላሴ የአዲስ አበባ ልጅ ነው። እናቱና አባቱ የአድዋ ተወላጆች ናቸው። ቤተሰሰቦቹ ከአድዋ ቢሆኑም እምቢ ለጎሳ ፓለቲካ በማለት ከሕወሃት ጋር አልተባበርም በማለቱ፣ በእነ በረከት ስሞዕን ትዕዛዝ በለሊት በፓሊስ በፌሮ ብረት ተደብድቦ የሞተ መስሏቿው ወደ ወንዝ ተጥሎ ነበር።

ምልዕቲ ኪሮስ፣ የለታይ ልጅ፣ ጋዜጠኛ አርአያ ስላሴ፣ በድፍኑ የአዲስ አበባ ልጆች በመንደር ለታጠሩት መንደርተኞች ለእነ መለስ፣ ለእነ ጃዋር፣ ለእነ ….በፍጹም አንገባቸውም። የአዲስ አበባ ልጅ እንዴት ከጎሳ በላይ ሊሆን እንደሚችል ለመገንዘብ ከአቅማቸው በላይ ነው። እድገታቸው፣ ትውልዳቸው፣ ስሪታቸው፣….አዲስ አበቤን በቅጡ እንዲረዱ አያስችላቸውም። የሸገር ልጅ “ዘር ለገበሬ” ነው ሲል ተራ መመጻደቅ የሚመስላቸው ለዚህ ነው።

የአዲስ አበቤን ስሜት የሚያውቁት የሚጋሩት የሚረዱት ከተማ ያፈራቸው፣ ከተሜዎቹ የድሬ፣ የናዝሬት፣ የሃዋሳ፣ የሀረር፣ የደብረዘይት፣ ….ልጆች ናቸው።

መለስ ዜናዊ አስመራን ሻዕቢያ እንደተቆጣጠረ፣ አስመራ ስቴዲዮም ላይ ባደረገው ንግግሩ እናንተም ላይ ያለው የጀርባ ጠባሳ እኔም ጋር ስላለ እረዳችኋለሁ ብሎ ደሰኮረ።

አዲስ አበቤዎች ላይ ያለው የጀርባ ጠባሳ ችግር መከራ እንግልት አድልዎ፤ ድሬዎች፣ ሀረሮች፣ ናዝሬቶች፣ ሃዋሳዎች፣….ላይም ስላለ ካለ ጥርጥር ይረዱናል።

ለዚህም ነው የጋራን ችግር በጋራ ለመቅረፍ፣ የከተማ ልጆች ትስስርና ትብብር የግድ የሚያስፈልገው። ፍጥነት ያለው ለውጥ እንዲመጣ ከተፈለገ ትብብሩና ትስስሩ ወደ “የከተሜዎች ንቅናቄ” ወይም “በከተሜዎች የሚመራ ትግል” ማደግ አለበት።

 

Related:
የአዲስ አበባ ቆይታዬና ትዝብቴ (ክፍል-1)

የአዲስ አበባ ቆይታዬና ትዝብቴ (ክፍል-2)

የአዲስ አበባ ቆይታዬና ትዝብቴ (ክፍል-3)

guest

0 Comments
Oldest
Newest Most Voted
Inline Feedbacks
View all comments

0
Would love your thoughts, please comment.x
()
x