Afar and Kunama

ያጣነው የባህር በር ብቻ ሳይሆን፣ የአፋርና የኩናማ ህዝቦችን ጭምር ነው

በአበራ ገ/ማርያም

የመለስና የሕወሃት ሴራ በኢትዮጵያ፣ በአማራና በኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስትያን ላይ ተዘርዝሮ ማለቂያ የለውም። አንዳንድ የዋሆች እንደሚያስቡት ሳይሆን መለስ በቀረፀው ህገ መንግስት የትግራይ ህዝብን አናሳ ፣ የዘለቄታ ደህንነቱን ገደል ከቶ ነው የሞተው። ምክንያቱም የመለስ ዋና መገለጫው የትግራይ ህዝብን ደህንነት ማረጋገጥ ሳይሆን፤ ካንሰር ሆኖ ለሞት የዳረገው ለኢትዮጵያ፣ ለአማራና ለተዋህዶ ያለው ወደር የለሽ ጥላቻ ነው።

በዓለም ታሪክ ውስጥ አብዝቶ የሚጠላው አገር መሪ የሆነ ብቸኛው ግለሰብ መለስ ዜናዊ ነው። ኢትዮጵያ እንደ ድርጅት ሕወሃት ላይ፣ እንደ ግለሰብ ደግሞ መለስ እጅ ላይ በፍጹም መውደቅ አልነበረባትም። ባጭሩ መለስና ሕወሃት በአጠቃላይ ኢትዮጵያ ላይ በተለይ ደግሞ የትግራይ ህዝብ የተላኩ የእግዜር ቁጣ ናቸው።

ሶማሌ ላንድ ከሱማሌ ተገንጥላ እራሷን የቻለች፣ የተረጋጋች፣ ምርጫ የምታካሂድ፣ ነጻ አስተዳደር ከመሰረተች ወደ 30 ዓመት ገደማ ሆኗታል። ነገር ግን በቅርቡ ከእስራኤል እንደ ሀገር እውቅና ከማግኘት ውጪ፣ ነጻ አገርነቷን የተቀበለ ሌላ ሀገር እስከ አሁን ድረስ የለም።

ወደ ኤርትራ ስንመጣ፣ መለስ ዜናዊ፣ እንደ የሽግግር መንግስት መሪነቱ ካለምንም ውክልና/ማንዴት፣ ኤርትራ ካልተገነጠለች ብሎ ለአፍሪካ አንድነትና ለተባበሩት መንግስታት ደብዳቤ ባይጽፍ ኖሮ፣ የኤርትራም እጣ ፈንታ የሶማሌ ላንድ ነበር የሚሆነው። መለስ ለኤርትራ ተገንጣዮች ትልቅ ባለውለታ ነው።

በእርግጥ ኢትዮጵያ የባህር በር ያጣችው በመለስ ሴራ ነው። ከኦነጉ ዲማ ነጎ እስከ ብአዴኑ ታምራት ላይኔ ፣ ከብርሃኑ ጁላ እስከ ባጫ ደበሌ፣ ከሬድዋን ሁሴን እስከ ጻድቃን፣…. ኢትዮጵያ በመለስ ሴራ የባህል በር እንዳጣች በቲቪ መስኮት ብቅ እያሉ እየነገሩን ነው።

አብይም በመንግስት ደረጃ ትኩረት ሰጥቶ የባህር በር ጥያቄ እያራገበ ያለበት የራሱ ድብቅ ፍላጎት እንዳለው አያጠራጥርም። አብይና ስርዓቱ ከማንም በላይ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ስጋት ስለሆኑ፣ ቅድሚያ ትኩረት አብይን ማስወገድ ላይ መሆን አለበት። መጀመሪያ መቀመጫዬ እንደሚባለው ፣ የኤርትራ ህገ ወጥ አካሄድ ለጊዜው በይደር መቆየት አለበት።

ነገር ግን አብይ የራሱን ድብቅ ውስብስብ ዓላማ ለማሳካት ቢሆንም የባህር በር ጥያቄን የሚያራግበው ፣ አብይና ስርዓቱ
የባህር በር ጥያቄ ሲያነሱ ከዝምታ በላይ ሄደን መቃወም የለብንም። ለምን?

ሲጀምር ይሄ አጀንዳ አሁን በአብይ ተራገበ እንጂ የእኛ ኢትዮጵያኖች አቅም በማጣት ተዳፍኖ የቆየ አጀንዳ መሆኑን ምንግዜም መርሳት የለብንም። ፕሮፌሰር አስራት የሰኔ 24 ኮንፈረንስ ላይ ለኢሳያስና ለመለስ ይሄ የእብሪት አካሄድ ይዞ የሚመጣውን መዘዝ አመላክተዋል። የኤርትራ ተወላጆችን ጨምሮ ብዙ ምሁራኖች የሂደቱን ህገ ወጥነት ለአፍሪካ ህብረትና ለተባበሩት መንግስታት አቤቱታ አቅርበዋል። በጊዜው የተባበሩት መንግስታት ዋና ጸሃፊ የነበረው ግብጻዊው ቡትሮስ ቡትሮስ ጋሊ አዲስ አበባን ሲጎበኝ፣ የኤርትራን ህዝበ ውሳኔ ህገወጥነት ለማሳሰብ ሰልፍ የወጡ የአዲስ አበባ ዩንቨርስቲ ተማሪዎች በግፍ ተገድለዋል። የኤርትራ አፋሮች አፋርን ለሁለት ስለሚከፍልና ኢትዮጵያዊነታቸውን ስለሚገፍ ተቃውሞ አሰምተዋል። ኢዴፓ ከ700,000 የሚበልጡ በመላው ዓለም ተበትነው የሚኖሩ ኢትዮጵያኖችን ፊርማ አሰባስቦ ለአፍሪካ ህብረትና ለተባበሩት መንግስታት የባህር በር ይገባኛል ጥያቄን አንስቷል። ሻዕቢያ ‘ትንሿ ኢትዮጵያ’ እያለ የሚያሽሟጥጣቸው የኩናማ ህዝብ ተቃውሞውን አሰምቷል።የመጀመርያው የጀብሃ ኮማንዶ ሰልጣኝና ” ደም የተከፈለበት ባርነት” መጽሃፍ ደራሲ ረዘነ ሃብተ፣ በኢትዮጵያዊነታቸው ካላቸው ጽናት የተነሳ ከአፋርና ከኩነማ የሻዕቢያን ትግል የተቀላቀሉት ከጥቂት ሰዎች አይበልጡም ብሎ ገልጿል።

ሕወሃት ስልጣን የያዘ ሰሞን፣ ኢትዮጵያን፣ ኢትዮጵያዊነትንና የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላም ቀን ከለሊት በሚያበሻቅትበት ወቅት፤ የአፋር መንፈሳዊ መሪ ስልጣን አንፍሬ አሊሚራ እንኳን አፋሮች ግመሎቻቸው ከኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ ጋር ያላቸው ቁርኝት በኩራት ተናግረዋል።

በደርግ ጊዜ መንግስት ለኩናማ ህዝብ ስኳርና ጠመንጃ ብቻ ነበር የሚሰጣቸው። መላ ኤርትራ ሻዕቢያ እጅ እስኪወድቅ ድረስ፣ ኩናማዎች አካባቢያቸውን እራሳቸው ነበሩ ከሻዕቢያ ጥቃት ሲጠብቁ የነበሩት።

የኢትዮጵያዊነት ጥንካሬ ያልገባው፣ ነገን ማየት ያልቻለው በረከት ስምዖን በአንድ ወቅት ደረቱን ነፍቶ አሰብን የማያስታውስ ትውልድ ፈጥረናል ብሎ ሲመጻደቅ ነበር። ኢሳያስና መለስም አዲስ ታሪክ የኤርትራን ጉዳይ ዘግተን ጽፈናል ብለው ደስኩረዋል። የጌቶቹን ፊትና ሆዱን አይቶ የሚንቀሳቀሰው ሬድዋን ሁሴንም፣ ዛሬ አሰላለፉን ከአብይ ጋር አስተካክሎ የባህር በር ጠበቃ ሆኖ ቀርቧል።

አሁንም ገና ኢትዮጵያ ላይ የተሰራው ግፍ ያልገባቸው፣ ኤርትራ ከህግ ውጪ ኢትዮጵያን በሚጎዳና ባዋረደ መልኩ እንደተገነጠለች፣ የኤርትራ ብሄረተኝነት ፀረ ኢትዮጵያ እንደሆነ ገና ያልገባቸው፣ ኤርትራን እንደ ነጻ ሉዓላዊ አገር ቆጥረው ጥብቅና ሲቆሙ፣ ሲሞግቱ እየታዘብን ነው።

እነ ዶ/ር አክሊሉን፣ ብላታ ሎሬንሶን፣ ዘርአይደረስን ያፈራች ኢትዮጵያ፣ እንዲህ አይነት ከዛሬ ፓለቲካ በላይ ተሻግረው ነገን የማያዩ የፓለቲካ ድኩማኖችን አፍርተናል።

ስለዚህ ከጎበዝን የአብይን ስርዓት የሚወገድበትን ቅድሚያ ሰጥተን እየሰራን፤ ጎን ለጎን ደግሞ ከኋላ ሆነን በባህር በር ጥያቄ ግፋ በለው ልንለው ይገባል። አብይ ለጦሩ፣ ደህንነቱ፣…..ለኢትዮጵያ ህዝብ በሙሉ በሚቆጣጠረው ሚድያ፣ የእኛን የነገን አጀንዳ እያስተዋወቀልን ስለሆነ ልንቃወም አይገባም።

ባይሆን ማሳሰብ ያለብን ጥያቄው የባህር ብቻ ሳይሆን፣ መላ ኤርትራ የሄደችበት መንገድ ከህግ ውጪ የኢትዮጵያን ብሄራዊ ጥቅም እንዲጎዳ ተደርጎ እንደሆነ መናገር ያስፈልጋል። ኢትዮጵያዊነቱን በጉልበት ተነፍጎ በደጋው ትግርኛ ተናጋሪ “ኤርትራዊነት” ለተጫነባቸው ለአፋርና ለኩናማ ህዝብ ድምጽ ልሆናቸው ይገባል።

የኤርትራ ብሄረተኞች የትግላቸው ዋና ምክንያት ፌዴሬሽኑ በሴራ ከህግ ውጪ ፈረሰብን ነው። ፌዴሬሽኑ የፈረሰብን በሴራ ነው ከሚሉት የሻዕቢያ ምክንያታቸው ጋር ሲነጻጸር፣ መላ ኤርትራ ከኢትዮጵያ የሄደችው አይን ባወጣ ሴራ ስለሆነ፣ ኢትዮጵያኖች የምናነሳው ጥያቄዎች ፍትሃዊም ህጋዊም ናቸው።

እውቁ የጦቢያ መጽሄት አምደኛ ሃሰን ዑመር አብደላ በአንድ ወቅት እንዳሉት፣ ልክ እንደ ጀርመንና የመን ሰኔና ሰኞ እስኪገጣጠሙ ድረስ፣ የኤርትራን ጉዳይ የመጨረሻ ፍትሃዊና ህጋዊ እልባት ለመስጠት ሁሌም ህሊናችን ዝግጁ ሆኖ በተጠንቀቅ መቆየት አለብን።

Related:

Eritrea’s Port Dilemma: Why Assab and Massawa Struggle to Attract Major Investment

guest

0 Comments
Oldest
Newest Most Voted
Inline Feedbacks
View all comments

0
Would love your thoughts, please comment.x
()
x