እኛ ዛሬ የጠፋን ምንድነው? በአንድ ትውልድ ከአልበገር ባይነት ወደ አጎብዳጅነት
በያሬድ ኃይለመስቀል
ጥዋት ተነስቼ የራስ መስፍን ስለሺን ታሪክ ደግሜ ማንበብ ስጀመር በአይነ ህሊናዬ ኢትዮጵያን ወደ 1920ዎቹ ተመልሼ ለማየት ሞከርኩ። በጣት የሚቆጠሩ አንደኛ ደረጃ የፈረንጅ ትምህርት ቤቶች ተከፍተው ማስተማር ጀምረዋል። የዛሬው ዮኒቨርስቲዎች፤ ባለ ማስተርስ ባለ ፒኤችዲ፤ ባለ ፕሮፌሰር መአረግ ሰዎች ኢትዮጵያ አልነበራትም። የፈረንጅ ጽሁፍ አንብቦ መረዳት የሚችለው ሰው በጣት የሚቆጠር ነበሩ።
አለም ደግሞ አፍሪካን ከሰው በታች ከዝንጀሮ ትንሽ ሻል አድርጎ መድቦ ሰውነታችንን የሚጠራጠርበት ዘመን ነበር። የነበረው ትምህርት የሀገር ውስጥ የቤተ ክርስቲያን ትምህርት ብቻ ነበር። እንግዲህ በዛን ግዜ አድገው ገና በ20 እድሜ ውስጥ እያሉ ጣልያን በ1929 ኢትዮያን ወረረች። ሸክሙ በነዚህ ወጣቶች ላይ ወደቀ። አክሊሉ ሀብተወልድ የ26 ዓመት ወጣት ነበር። እነ ሻለቃ መስፍን ስለሺ እንዲሁ በ20ዎቹ ውስጥ የነበሩ ወጣቶች ነበሩ። ንጉሰ ነገስቱ እራሳቸው ሲነግሱ በ30ዎቹ እድሜ ነበሩ፤ የሀገር ትምህርት እንጂ በፓለቲካ ሳይንስ ፒኤች ዲ፤ ማስተርስ ወይ ዲግሪ አልነበራቸው።
ከዛ ወደ ኋላ ስሄድ ኢትዮጵያ ፈርሳ እንደገና በማሰባሰቡ ላይ ቆርጠው የተነሳው የቋራው ካሳ ሀይሉ /ቴዎድሮስ/ እንዲሁ ሀገርን አንድ የማድረግ ዘመቻ ሲጀምር የ24 ዓመት እድሜ ነበረው።
የመጀመሪያው ጥያቄ ሩቅ ሳንሄድ እንዴት ኢትዮጵያ እንደ አጼ ቴዎድሮስ ያለ ቀድሞ የሚያስብ አደጋ መምጣቱን ቀድሞ ተረድቶ ሀገርን አቅምን በማሰባሰብ ከኦቶማን ቱርክ፤ ከግብጽ እና ቦሀላም ከጣልያን እራስን ለመከላከል የሚያስችል አቅም መፍጠርን ተጣደፈ?
ከዛ ደግሞ እንደ አጼ ሚኒሊክ የሰውን የስነልቦና ድክመቶች ተረድቶ በፍቅርም በጥቅምም በጉልበትም የሚያስተባብርና ሀገርን ከአንድ ገናና የኢሮፕያ ቅኝ ገዢ ለማዳን የረቀቀ ጥበብ፤ ዲፕሎማሲ፤ ወታደራዊ ዝግጅት፤ በስለላና አና በማደናገርን እንዴት ድል ለመምታት ቻሉ? ወጣት ሚኒሊክን ማን አስተማረው? ማን አሳየው? እንዴት መረዳትና የመተግበር አቅም ገነባ? የሚሉት ጥያቈዎችን ስነሳ ሚኒሊክን የፈጠረውን ንጥረ ነገር አሁን እንዳለ አላውቅም። የኔ እድሜ ከነዚህ ሰዎች እጥፍ ነው። በኢትዮጵያ ፓለቲካ ውስጥ ደግሞ 60 ዓመት አጥፍተው እዛው የተነሱበት ቦታ ያሉ አሉ?
እንደ አጼ ኃይለስለሴ ያሉ ፈረንጁንም ጥቁሩንም በብልጠትና በማሳመን አንድ ጥይት ሳይተኩሱ ለመቶ ዓመታት ሲቀማ ሲመለስ እንደገና ሲቀማ የቆየውን የኢትዮጵያን ቀይ ባህርን በምን ጥበብ አስመለሱ? በምን ብልሀት ከእንግሊዝ ጉሮሮ ትግራይን ነጥቀው ማውጣት ቻሉ? ከዛም በትዕግስትና በብልሀት እንዴት የኦጋዴንን፤ የጋንቤላን አንድ ጥይት ሳይተኩሱ አስመለሱ?
ምናልባትም ደርጎችና አብዮተና ነን ያሉ ተማሪዎች ተጣድፈው ባይገሏቸው ኖሮ ጅቡቲን እና ከሰላን ወደ ኢትዮጵያ ያስመልሱ ነበር። አሁን የምትታመሰው ሱማሌ ላንድም ከኢትዮጵያ ጋር ልቀላቀል ብላ ጠይቃ አይ አትቸኩዪ በብልሀት በይደር ተይዞ እያለ ነው የተገደሉት (በሶደሬ በንጉሱ ቤተመንግስት የሱማሌላንድ መሪዎች በሚስጥር መጥተው ከቀዳማዊ ኃይለስላሴና ባለሟሎቻቸው ጋር ያደረጉትን ጥያቄና ድጋፍ ደጃዝማች ወልደሰማዕት ጽፈውታል)።
ከዛ ወረድ ስንል ደግሞ እንደነ አክሊሉ ሀብተወልድ፤ እነደነ ከተማ ይፍሩ፣ እነደነ ዶ/ር ምናሴ ያሉ የረቀቁ የዲፕሎማሲ ሰዎች፣ እንደነ ከበደ ሚካኤል፤ አፈወርቅ ተክሌ፣ አዲስ አለማየሁ፣ ጸጋዬ ገብረመድህን፤ መንግስቱ ለማ፤ እስክንድር ቦጋስያን፤ ጥላሁን ገሰሰ፤ሙላቱ አስታጥቄ፤ ያሉ የኢትዮጵያ የሞራል ፍልስፍና ፈጣሪዎች ከየት መጡ ምን ፈጠራቸው? እንዴት የምናቡን አለም ወደ ገሀድ እውነተኛው አለም ማምጣት ቻሉ? የሚለው ነው።
እነዚህ ሰዎች ጥይት ሳይተኩሱ ጦር ሳያሰብቁ ኢትዮጵያን አንድ አድርገው አስተባብረው አስፍተው አበልጽገው አስከብረው አለፉ? እነዚህ ሰዎች የምን አይነት የመንፈስ ምግብ ተመግበው አደጉ? ለምን ይህ ሁሉ ፕሮፌሰር እና ዶክተር እያለ አንድ አክሊሉ ሀብተወልድ እናቶች መውለድ አቆሙ? እንደዚህ እንደ ሙጃ ያደገውና በየጎጡ ባለ ፒኤች ዲና ባለ ፕሮፌሰር ካባ የለበስው ተናግሮ ማሳመን፤ ሞግቶ መርታት አቃተው?
እንዴት የነገው ትውልድ የሚያስታውስበት ፍሬ ጥሎ ማለፍ አቃታው? ለምን ኢትዮጵያ በአንድ ትውልድ ፍሬ አልባ ሆነች? እንዴት ለብዙ ሺ ዘመን ስልጣኔ የገነባ ህዝብ በአንዴ ተመልሶ ወድ ጎጥ፤ ሀይማኖት፤ ማረድ፣ መስለብ። ዛፍ ቅቤ መቀባት ተመለሰ?
በወታደራዊ መስክ ደግሞ ሞሶሎኒ ሰውን እንደ ትንኝ በዲዲቲ መግደልና ማጥፋት የሚችለውን ሀይል እኛ የማንችለውን ጠላት መጥቶብናል እና አርፈን እንቀመጥ፣ እያረስንና ዶሮ እያረባን እንቁላላችንን ለጣልያን እየሸጥን አርፈን እንቀመጥ አላሉም። ጠመንጃቸውን አዘቅዘን በሰላም እንገዛ አላሉም። ንጉሰ ነገስት ሳይኖራቸው፣ የአለማቀፍ ድጋፍ ሳይዙ፣ ጠመንጃና ጥይት ማምረት ሳይችሉ ብዙዎቹ እንድ እራሳቸውን ይዘው ጣልያንን ተዋግተን እናባርራለን የሚል መንፈስ ከየት አምጥተው ወደ ጫካ ገቡ? ይሄንን እብደት የሚመስል ድፍረት ምን አይነት የመንፈስ ምግብ ተመግበው ቢያድጉ ነው እንዲህ አይነቱን ጋራን የመግፋት ያህል የከበደ የሚመስለውን ሀይል ጥቂት ጓደኞች እየሆኑ የገጠሙት?
ዘጠና በመቶ የሚሆነው የአፍሪካ እና ህንድ ሀገር እኮ በጠመኝጃ አይደለም ቅኝ የተያዘው። የኢሮፓውያን ነጋዴዎችና ሚሴናዊያን እየሄዱ ባላባቶቹን እያሳመኑ በገንዘባቸው ሀገሩን እየገዙ ነው። እዚሁ አጠገባችን ያለችው ሱማሊያን እንዴት ባላባቶቹ እየተጫረቱ ለጣልያን፤ ለእንግሊዝ አና ለፈረንሳይ ሀገራቸው እንደሸትጡ የሚያሳይ የፈረሙበትን ውሎች እና የተከፈላቸውን ገንዘብ መጠን የሚያሳያቸውን ዝርዝር ውሎችን ጠርዞ አንድ የሱማልያ ምሁር አሳትሟል። “The Scramble in the Horn of Africa” by Mohamed Haji Mukhtar በሚል ጥራዝ ወጥቷል። የኛን ጅቡቲ ሳይቀር እየሸጠው ባላባት ስም፤ ምን ያህል እንደተቀበለ ተመዝግቧል።
ታድያ እዚህ ሀገር ቀርመው የኖሩ እንዴት የነጻነትን፤ የአንድነትንና የመስዋዕትነትን ዋጋ አወቁ?
ታድያ የአፍሪካ ገዢዎች የራሳቸውን ሀገር በፓወንድና በሊሬ ሲቸበችቡ የኛ እንደነ ራስ መስፍን ስለሺ፤ እነ ራስ አበበ አረጋይ፣ራስ ደስታ ዳምጠው፣ልጅ አበራ ካሳ፣ ልጅ ሀይለማሪያም ማሞ፣ ልኡል ወንድወሰን ካሳ፣ ገረሱ ዱኪ፤ ጃገማ ኬሎ፤ ደጃችማች በላይ ዘለቀ ያሉ ሰዎች ምን ፈጠራቸው? ምን አይነት የመንፈስ ምግብ ተመግበው ነው ጣልያንን እናሸንፋለን ብለው ወደ ጫካ የገቡት? ሰውን እንደ ትንኝ በፍሊት የመጨረስ አቅም ያለውን ሀይል እናሸንፋለን ብለው ማሰባቸው እብደት አይመስልም።
መሪ ኖረ አልኖረ፣ ንጉስ ኖረ አንልኖረ፣ ጳጳስ ኖረ ሞተ እነሱ ያለ መሪ በራሳቸው መተማመን እንዴት አደረጁ? እንዴት ይሄንን የመንፈስ ጥንካሬ ከየት አገኙት ብለን መጠየቅ ያሻል?
ይህ የመንፈስና፤ የአካልና የእውቀት ጥንካሬ ምንጩ ምንድነው ብለን መጠየቅና ከዛ ይሄንን ጥንካሬ የሚሰጠንን ነገር ማፈላለግ እንችላለን።
አውጥቼ አውርጄ ሳስበው በኛና በእነሱ መሀከል ያለት የፈረንጅ ትምህርት ነው። ሁሉም ትምህርት አላማ አለው። ለኛ የተሰጠን የበታችነታችንን እንድንቀበል፣ ኃላ ቀር ነው፤ የበታች ነን ብለን እንድናስብ ተቀምሞ የተሰጠን ነው። ፕሮፌሰር ብለውንም ብቁ ነን ብለን አናስብም።
የሀገሩ ትምህርት እውነት ለመናገር መተማመን ብቻ ሳይሆን በውስጡ ምንም ነገር አይሳነንም የሚል እሳቤ ነበረው።
ሁለተኛ እምነት ነው። እነዚህ ሰዎች በራሳቸውና በፈጣሪያቸው አሸናፍነት ምንም ጥርጥር አልነበራቸውም። ቢሞቱም በትንሳኤ በደስታ እንነሳለን የሚል እምነት ነበራቸው። ውርደትን እንጂ ሞትን አይፈሩም ነበር።
ሶስተኛ አስፍቶ እና አርቆ ማሰብ፣ ማየትና ማካተት ነው። ወጣት ካሳ ሀይሉ/ቴዎድሮስ ከሰላ ሄዶ ኦቶማንን ጦር ገጠመ። እሱ በፈረስ፤ በጎራዴ፤ በቆመህ ጠብቀኝ ተመንጃ እነሱ ደግሞ በመድፍ። በመድፍ ተሸነፈ። ወደ ጎንደር ተመለሰ። ይህቺ መድፍ አይኑን ከፈተችለት። ኢትዮጵያ በዘመነ መሳፍንት ተከፋፍላ ከቆየች ልክ እንደ ከሰላ ቀስ በቀስ ግዛቷን ኦቶማን ተርክ ይወስደዋል ብሎ አሰበ። ስለዚህ አሰባስቦ አንድ ጠንካራ ሀገር ለመመስረት ወሰነ። ሁለተኛ አለም ተቀይሯል ስለዚህ እሱ በጦርና ጎራዴ እነሱ በመድፍ ጦርነት እንደሆነ ገባው። ስለዚህ መድፍ ለመስራት ህይወቱን ሰጠ።
የኢትዮጵያ የዘመናዊ ትምህርት በራስ መተማመንን፤ አጎብዳጅነትን፤ ታዛዥነትን ፈጠረ። ዛሬ ብዙ ሺ ፕሮፌሰርና ዶክተር በፓለቲካ ሳይንስ ይዟል ይሁንና አንድ የ26 ዓመት የቄስ ልጅ የነበረው የአክሊሉ ኃብተወልድ የመዋጋት መንፈስ አልሰጠውም። ጣልያን ሀገራችንን ይዛ አክሊሉ ፓሪስ ላይ ባለ ሁለት ክፍል አፓርትመንቱን ተከራይቶ አንዷን ቢሮ አድርጎ የኢትዮጵያን ሰንደቅ አላማ ሰቅሎ ኤንባሲ አድርጎ ነጻ የኢትዮጵያ ግዛት ብሎ ፓስፓርት ይሰጥ ያድስ ነበር። ኢትዮጵያ ነጻ ግዛት እስካላት ድረስ ነጻ ገገር ናት የሚል ጽኑ እምነት በዚህ ወጣት ልብ ውስጥ ምን ፈጠረው? አክሊሉ ኢትዮጵያን ወክሎ በፓሪስ ቤተ መንግስት ተጋብዞ ሳለ በአልፋቤት መቀራረብ የጣልያን አንባሳደር ቅርቡ ነበርና ቦቅስ ገጥሞ በገላጋይ ነው የጣልያኑ አንባሳደር የተረፈው። ይህ ተረት ተረት ሊመስላል። ዛሬ የትኛው ኢትዮጵያዊ ቦቅስ ቀርቶ ጮክ ብሎ መናገር የሚደፍረው። ታድያ እንዲህ ቅስሙ የተሰበረ ህዝብ በአጨር ግዜ የፈጠረው አስተምህሮ ምንድነው።
ለዛሬው እኔስ ብለን ሁላችንም እራሳችንን እንጠይቅ።
ያሬድ ኃይለመስቀል