Abiy Ahmed and Issayas Afewrki

አይቀሬ በሚመስለው የአብይ እና ኢሳያስ ጦርነት ላይ የፋኖ አቋም ምን ይሁን?

የአብይና የኢሳያስ ጦርነት አይቀሬ ይመስላል። አብይም ኢሳያስም ወደ ጦርነቱ የሚገቡበት የየራሳቸው አስገዳጅ ምክንያቶች ይኖራቸዋል። ጦርነቱ ኢምሬቶችን፣ ሳውዲዎችን፣ ቱርኮችን፣ ግብጾችን የመሳሰሉ ቀጠናዊ ኃይሎች እንደሚሳተፉበት ግልጽ ነው። ፋኖም የበይ ተመልካች ከመሆን ባሻገር፣ ወደ ጦርነቱ ተገዶ የሚገባበት ምክንያቶች ብዙ አሉ።

ከአብይ ኦሮሙማ በላይ በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያ የብሄራዊ ህልውና ስጋት የለም። አብይ አንድ ቀን በቆየ ቁጥር ኢትዮጵያን ይበልጥ ቅርቃር ውስጥ ይከታታል። ስለዚህ አብይን ከስልጣን በአጭር ጊዜ ውስጥ ለማስወገድ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎችን የሚወክሉ ሰፊ መሰረት ያላቸው ኃይሎች ትብብር ከምንግዜውም በላይ አሁን ላይ አስፈላጊ ነው።

ጦርነቱ ከተነሳ የፋኖ መሪዎች፣ ተዋጊዎችና ደጋፊዎች አቋም ምን ቢሆን ይመረጣል? ለምን? የተለያዩ ነጥቦችን እንቃኝ።

፩. ትብብር

በጂዖ ፖለቲካዊ ጥቅማቸው ተፃራሪነት እና በሚያራምዱት ርዕዮተ ዓለም ተቃርኖ የተነሳ ሊጠፋፉ የሚፈላለጉት የነበሩት፣ ብርቱዎቹ የሶቭየቱ ጆሴፍ ስታሊንና የብሪታንያው ዊንስተን ቸርችል፡ የጋራ ህልውናቸው አደጋ የነበረውን የጀርመኑን ናዚ ሂትለርን ለማስወገድ ከመተባበር ውጪ ምንም አማራጭ እንዳልነበራቸው ተገንዝበው፣ ተባብረው ሂትለርን አስወግደዋል። በርሊንን በሁሉም አቅጣጫ ከበው ተቆጣጥረው የሂትለርን ሥርዓት ባስወገዱ ምሽት ግን፤ አንድ ላይ የሚያቆማቸው አጀንዳ በማለቁ፣ ጀርመንን ሁለት ቦታ የሚከፍል የበርሊን ግምብ መገንባት ተያይዘው ዓለምን ወደ ቀዝቃዛው ጦርነት፤ ወደ ምስራቅ ምዕራብ ክፍፍል ከተቱት።

ከዚህ ታሪካዊ ክስተት የሚታየው፣ ፋኖም የሚሰራውን ጠንቅቆ እስካወቀ ድረስ፣ ከሻዕቢያና ከወያኔ ጋር የአብይን ኦሮሙማ ለመጣል በጊዝያዊነት ቢሰራ ችግር እንደሌለው ብቻ ስይሆን፣ መስራትም ሊኖርበት እንደሚችል ነው።

ነገር ግን የተፈጥሮ ባህሪያቸው አብሮ ለመዝለቅ ስለማይፈቅድላቸው፣ በጊዚያዊነት አብሮ መስራት ከታሰበ፣ በጥንቃቄ ሊጤን የሚገባው ጉዳይ አለ።

ይህም፡ አጋርነት፣ ትብብር ወይም አብሮ መስራት በተለያየ መንገድ ሊዋቀር የሚችል መሆኑ ነው። አብሮ ለመስራት የሚስማሙት አካላት፣ በእኩልነት ወይስ በተለያየ እርከን ሆነው ነው የሚተባበሩት? የሚለው ጥርት ተደርጎ ሊታወቅ ይገባል።

  • ፋኖ ከሚቆጣጠረው የሃገሪቱ ክፍል ብዛት እና በተለይም የፋኖ የድጋፍ መሰረት (Support base) በእጅጉ የሰፋ ከመሆኑ አኳያ፣
  • ሻዓቢያ ኢትዮጵያዊ ሃይል እንዳለመሆኑ መጠን እና የኢትዮጵያን ዕጣ ፈንታ እንዲወስን ሊፈቀድለት ስለማይገባ፤
  • ትህነግም ኢትዮጵያዊ በሆኑ ሰዎች ቢመራም፣ የዘለቄታ ውጥኑ ኢትዮጵያን ማፍረስ መሆኑ ግልፅ ስለሆነ፤

የኢትዮጵያን የወደፊት ዕጣ ፈንታ የመወሰን ከፍተኛ ተፃዕኖ ባለው በዚህ ትንቅንቅ ውስጥ ኢትዮጵያዊ የሆነው እና ከሁሉም በላይ የኢትዮጵያውያን ድጋፍ ያለው ፋኖ የትብብሩ “ላዕላዊ” ዐባል ሆኖ ሻዕቢያና ወያኔ አንድ ላይ ተደምረው “ታኅታዊ” የፋኖ አጋር ድርጅቶች (Junior Partners) እንዲሆኑ መደረጉ እጅግ ወሳኝ ነው።

ይህ በቃላት ለመግለፅ ከሚቻለው በላይ ዐብይ ጉዳይ ነው። ይህ እንዴት ሊዋቀር ይችላል? ድርድሩ በምን ሁኔታ ይኪያሄዳል? ምን ያህል ጊዜ ይፈጃል? እና የመሳሰሉት ጥያቄዎች እንደፋኖ መሪዎች ብቃት እና ብስለት ይወሰናሉ።

ፋኖ ቢያንስ ጎጃም፣ ወሎን፣ ጎንደርንና ሸዋን በአብኛው እየተቆጣጠረ ነው። ከጎጃም፣ ከወሎ፣ ከጎንደርና ከሸዋ ውጪ የሚኖረው አማራ ብዛቱ በ4ቱ ክፍለ ሀገሮች ውስጥ ከሚኖረው አማራ ይበልጣል። በተጨማሪም ከአማራው ውጪ በትህነግ እና በኦህዴድ ከተወናበዱ ጥቂት ወገኖቻችን በስተቀር የአቢይ አህመድ እና የግብረአበሮቹ ግፍአዊ አገዛዝ ያስመረረው የሁሉም ጎሳ ኢትዮጵያዊ ሁሉ የፋኖ ደጋፊ ነው።
በተለያዩ ከተሞች ከየቦታው መጥተው ተሰባጥረው የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ሁሉ የፋኖ የተፈጥሮ ደጋፊዎች ናቸው።

ስለዚህ ፋኖን የሚደግፈው ህዝብ ቁጥር ብዛት፣ የሚደግፈው ህዝብ የጂዮግራፊ ስፋት፣ የፋኖን ታሪክ፣ ፋኖ በከተሜው ሃብቱም እውቀቱም ባለው ህብረተሰብ ያለውን ሰፊ የህብረተሰብ ተቀባይነት ግንዛቤ ውስጥ ስንከት፣ ሻዕቢያና ወያኔ (በጥምረት 2 ክፍለ ሀገሮችን ብቻ የሚወክሉ ኃይሎች) የፋኖ ታኅታዊ አጋር ድርጅቶች ከመሆን ውጪ እድል ሊኖራቸው አይገባም።

ፋኖ የሚኒሊክ ልጅ ነኝ ካለ፣ እምዬ ሚኒሊክ የአውሮፓ ቀኝ ገዢዎች አፍሪካን እንደ ቅርጫ በሚቀራመቱበት ጊዜ እንኳን (even during the scramble for Africa) ፣ ጥቁር ህዝብ ብቻ ሳይሆን ህንዱና ቻይናው እንደ ዝንጀሮ በሚቆጠርበት ዘመን፣ እንደ አቻ ከአውሮፓውያን ጋር ቁጭ ብለው የተደራደሩ ልጆች መሆኑን መርሳት የለበትም።

ፋኖ የአጼ ኃ/ስላሴ፣ የከተማ ይፍሩ፣ የአክሊሉ ሀብተወልድ ልጅ ነኝ ካለ፣ አባቶቹ የቅኝ ገዥዎችን ሴራ በጣጥሰው በእሳት ተፈትነው የአፍሪካ ህብረትን እንደመሰረቱት፣ ፋኖ ቢያንስ የአፍሪካ ቀንድ አውራ አሰባሳቢ መድህን ኃይል ሆኖ መውጣት አለበት።

ስለዚህ የፋኖ የመሪነት ሚና ታሪኩን፣ ብዛቱን፣ ተደማጭነቱን ግንዛቤ ውስጥ የከተተ ሊሆን ይገባል።

፪. ሴራና ክህደት

የፋኖ መሪዎች፣ ተዋጊዎችና ደጋፊዎች አንድ መሰረታዊ ስህተት ከመስራት መጠንቀቅ አለባቸው።
የኤርትራ፣የወያኔና የኦነግ አውዳሚ ብሄረተኝነት ዋና መገለጫው ፀረ ኢትዮጵያ፣ ፀረ አማራና ፀረ ኦርቶዶክስ እንደሆነ ለአንድ አፍታም መዘንጋት ብዙ ዋጋ እንደሚያስከፍል ማወቅ አለባቸው።

የኢትዮጵያ/የአማራ/የተዋህዶ ጥላቻ ከውስጣቸው ከወጣ፣ የሻዕቢያ፣ የወያኔና የኦነግ ብሄረተኝነት የተፈጥሮ ሞታቸውን ይሞታሉ። ባጭሩ ይሄ ስር የሰደደ ጥላቻ ብቻ ነው በህይወት እንዲቆዩ የሚያደርጋቸው። ስለዚህ ከሻዕቢያና ከወያኔ ጋር ምናልባት በተጠኑ የጋራ አጀንዳዎች ላይ የአብይን የኦሮሙማ ስርዓት ለመጣል መተባበር ካስፈለገ ( ሊያስፈልግ ይችላል)፣ ትብብሩ አብይን ከመጣል ባሻገር እንደማይዘል፣ እንዲያውም ወደ እርስ በእርስ ጦርነት ውስጥ ሊገባ እንደሚችል ከአሁኑ የህሊና ዝግጅት መደረግ አለበት። መሬት ላይም ይሄን ግንዛቤ ያደረገ ስራ መሰራት አለበት።

ከቅርቡ የኦሮ-ማራ ትብብር ብንጀምር፣ ብአዴን ወያኔን ከመጣል ባሻገር የብሄር ፓለቲካንና ኦሮሙማን ምንነት በቅጡ ለመረዳት ልምዱም፣ እውቀቱም፣ ችሎታውም ስላልነበረው፤ ወያኔን ለመጣል የአምበሳውን ድርሻ ቢወስድም፣ የኦህዴድ ሴራ ሰለባ ሆኖ ቀረ።

ከአብይ ኦሮሙማ ጋር ሲወዳደሩ፣ ሻዕቢያና ወያኔ በኢትዮጵያ ጠላቶች በሴራ ተፈጥረው፣ በሴራ አድገው፣ በሴራ እንዳረጁ ይታወቃል። የብዙ ዓመት ሴራና የመጠፋፋት ልምድ አላቸው። ሻዕቢያና ወያኔ ከቀይ ኮኮብ ዘመቻ እስከ “ጽምዶ” በታሪካቸው ብዙ ጊዜ ተባብረዋል፣ ተከዳድተዋል፣ ተጠፋፍተዋል። ሻዕቢያና ወያኔ የኢህአፓን ሰራዊት ሳህልና አሲምባ ውስጥ ከማገት/ ከመጨፍጨፍ ጀምሮ ብዙ የኢትዮጵያ ተቃዋሚዎችን በተለያየ ጊዜ ከድተዋል፣ አስረዋል፣ ገድለዋል።

የፋኖ መሪዎችም የአብይ መንግስት እየወደቀ ነው ብለው ሲያስቡ፣ ሻዕቢያና ወያኔ ታሪካዊ ጠላታችን ነው ብለው የሚገምቱትን ፋኖን ለማጥፋት እንደሚተባበሩ አውቀው፣ ከወዲሁ የራሳቸውን ስትራተጂ ነድፈው ትብብር ውስጥ ሊገቡ ይገባል።

በትንሹ ወያኔ የጎንደርን መሬት ወልቃይትን፣የወሎን መሬት ራያን ለማግኘት ፋኖ ላይ እንደሚያሴር መርሳትም የለብንም። ሻዕቢያም ፋኖ የአባቶቹ ( የቴድሮስ/ የሚኒሊክ/የጎበና/ የአሉላ) ልጅ እስከ ሆነ ድረስ የአባቶቹን ግዛት ቀይ ባህርን እንደሚያስብ ይገባቸዋል።

፫. የጦርነቱ ቀጠናዊ ይዘት

በቅርቡ አብይ በኢምሬቶች ለሚደገፈው የሱዳኑ ፈጥኖ ደራሽ ጦር (Rapid Support Forces/RSF) የማሰልጠኛ ጦር ጎጃም/ቤንሻንጉል ውስጥ እንደሰጠ ተጋልጧል። በአብይና በኢምሬቶች መካከል ብዙ ሚስጥራዊ ስምምነቶች ከሌሉ፣ ኢምሬትስ አብይን በገንዘብ ይሄን ያህል የምትደግፍበት ምክንያት አይኖርም።

ይሄ የRSF ማስልጠኛ ሳውዲን፣ ቱርክና የሱዳኑን አል ቡህራን መንግስት ክፉኛ አስቆጥቷል። የሳውዲ፣ የቱርክና የኢሚሬትስ ልዑክ ቡድኖች በዚሁ ጉዳይ ለመነጋገር አዲስ አበባን ጎብኝተዋል።

ቀደም ሲል የመን፣ አሁን ደግሞ ሱዳን በቀጠናዊ የውክልና ጦርነት እየወደመች እየፈረሰች ትገኛለች። ይሄ የውክልና ጦርነት ከሱዳን ባሻገር ሳውዲ ኤርትራን ይዛ ኢትዮጵያ ውስጥ ለማስገባት ደፋ ቀና እያለች ነው። ቱርክና ግብጽም በተለያየ ምክንያት የዚሁ የውክልና ጦርነት ተሳታፊዎች ይሆናሉ።

ስለዚህ ፋኖን የመሰለ ኢትዮጵያዊ ኃይል፣ ይሄ ቀጠናዊ ይዘት ያለው ጦርነት እንደሆነ በቂ ግንዛቤ መያዝ ይገባል። በፋኖ አብይ ተዋናይነት የሚመሰረተው ቀጠናዊ ትብብር፣ አብይን ከማስወገድ ባሻገር ኢትዮጵያን እንደ ሱዳን ትርምስ ውስጥ እንዳይከታት ከወዲሁ በቅጡ መታሰብ አለበት።

ፋኖ በአንድ በኩል ሻዓቢያ እና ትህነግ በሌላ ሆነው አቢይን ለማስወገድ ቢቀናጁ ምናልባትም ከቀናት ባልበለጠ ጊዜ ውስጥ ከላይ የተጠቀሱት ቀጠናው ላይ የጂዖ ፖለቲካ ጥቅማቸውን ለማስጠበቅ የሚሯሯጡት ሃገራት እና ሃይላት ከፋኖ ጋር ሊኖራቸውን የሚገባውን ግንኙነት መስመር ለማስያዝ መምጣታቸው አይቀሬ ነው። ፋኖ ይህን ከወዲሁ አስቦ እንዴት ከነዚህ ሃይሎች ጋር እንደሚደራደር በቅጡ የታሰበበት ዕቅድ ሊያዘጋጅ ይገባል።

ፋኖዎች በዱር በገደሉ እየተንከራተቱ እየከፈሉ ካለው እጅግ አስደማሚ መስዋዕትነት በተጨማሪ ከላይ እንደተጠቀሱት ቀደምት ኢትዮጵያውያን በድርድር እና በዲፕሎማሲ የሚፈተኑበት ጊዜ የቀረበ ይመስላል።


Opinions expressed by contributors are their own. Ethiofact does not endorse and is not responsible for the accuracy of any of the views expressed in the content on this site.

guest

0 Comments
Oldest
Newest Most Voted
Inline Feedbacks
View all comments

0
Would love your thoughts, please comment.x
()
x