ሰላማዊ ትግልና የኮ/ል ደመቀ ዘውዱ መንገድ
በአበራ ገ/ማርያም
ኮ/ል ደመቀ ዘውዱ የወልቃይት ኮሚቴ መስራችና መሪ ናቸው። ካለማጋነን የወልቃይትን ትግል ከኮ/ል ደመቀ መነጠል፣ ክርስትናን ከክርስቶስ የመነጠል ያህል ነው። የወልቃይት ኮሚቴ በዘመነ ወያኔ እልህ አስጨራሽ የሰላማዊ ትግል አካሂዷል። አሁን ደግሞ ከሰላማዊ ትግሉ በተጨማሪ፣ ህዝቡን አንቅቶ፣ አደራጅቶ፣ አሰልጥኖ፣ አስታጥቆ፣ የተከዜ ዘብ ገንብቶ፣ ወልቃይትን ከማናቸውም የወያኔ ወረራ ለመመከት በንቃት እየተጠባበቀ ይገኛል።
ኮ/ል ደመቀ በአንድ ወቅት እንደተናገሩት፣ እንደ በፊቱ ወልቃይት በወያኔ ወራሪዎች ተይዞ አይደለም እያለቃቀሱ ያሉት። አሁን ላይ መሬታቸውን በእጃቸው ይዘው፣ እራሳቸውን በራሳቸው እያስተዳደሩ፣ ወልቃይትን በተከዜ ዘብ ከጥቃት እየተከላከሉ፣ በሁለ ገብ ትግል ለዘለቄታው ወደ ባለቤቱ እንዲመለስ እየሰሩ ነው።
የወልቃይት ኮሚቴ የወያኔን ህገ መንግስት ተከትሎ ለትግራይ ባንቱስታን ክልልና ለፌዴሬሽን ምክር ቤት አቤቱታ በተደጋጋሚ አቅርቧል። የኮሚቴው አባሎች ከወልቃይት እስከ ሱዳን፣ ከጎንደር እስከ አዲስ አበባ፤… እየታሰሩ፣ እየተሳደዱ፣ እየታፈኑ፣ እየተገደሉ፣ አንድም ቀን ከሰላማዊ ትግላቸው ሸብረክ ሳይሉ ለወያኔ ውድቀት ዋናው ምክንያት ሆነዋል።
ወልቃይት የወያኔ ጭካኔ፣ ክፋትና ግድያ ማሳያ ናሙና ናት። በጥቅሉ ወያኔ የወልቃይት ህዝብ ላይ ያደረሰው በደል የትም ኢትዮጵያ ውስጥ አልተፈጸመም።በስብሃት ነጋ ትዕዛዝ አዲስ አበባ መጥተው ለፌዴሬሽን ምክር ቤት አቤቱታ እንዳያስገቡ፣ እንጦጦ ላይ ኮሚቴው ታግቶ ወደ ስብሃነት ነጋ የግል እስር ቤት ተወርውሯል።
ኮ/ል ደመቀ ዘውዱ በነፍጥ ለማስወገድ ገዳይ ቡድን ከመቀሌ ወደ ጎንደር ከተማ ተልኳል። ሀምሌ 5 ቀን ኮ/ል ደመቀ ዘውዱ መኖሪያ ቤታቸውን የከበበውን የአጋዚን ቅጥር ነፍሰ ገዳይ በጀግንነት በመረፍረፍ የአፄ ቴዎድሮስ ልጅነታቸውን አስመስክረዋል። የጎንደር ከተማ ህዝብም ከጎናቸው ቆሟል። ገዱ አንዳርጋቸውም ኮ/ል ደመቀን ለወያኔ አሳልፌ አልሰጥም ብለው አኩሪ ታሪክ ጽፈዋል ።
ይህቺ ሀምሌ 5 ቀን የወያኔ ቅስም የተሰበረበት፣ የወያኔ የውድቀት የመጨረሻው መጀመሪያ ጉዞ ፍንትው አድርጎ ያታየበትና የአማራው የህልውና ትግል አዲስ ምዕራፍ ውስጥ የገባበት ቀን ነበር።
በዘመነ ወያኔ ባደረጉት ውስብስብ ትግል፣ ጎንደር ከተማ ላይ ባደረጉት ህዝባዊ ውይይት፣ የወልቃይትን ጉዳይ ከወልቃይቴዎች እጅ አውጥተው ቢያንስ የጎንደር ህዝብ አጀንዳ አድርገዋል። ቀጣይ ዓላማቸው ደግሞ ወልቃይትን የመላው አማራ ህዝብና የኢትዮጵያ ህዝብ አጀንዳ ማድረግ እንደሆነ በድፍረት ተናግረዋል። ብዙም ሳይቆይ “ወልቃይት ብረሳች፣ ቅኜ ትርሳኝ” የሚል የአማራ ህልውና ትግል ተወልዶ፣ ወልቃይት የትግሉ መሪ መፈክር ሆኗል። ዛሬ ወልቃይት ከአማራው አልፎ፣ የመላው ኢትዮጵያ ምናልባትም የምስራቅ አፍሪቃ አጀንዳ መሆኑን ብዙ ሰው ይቀበላል።
አሁን የወልቃይት ኮሚቴ የሚያካሂደው ውስብስብ ሰላምዊ ትግል ከወያኔ ጋር ብቻ ሳይሆን፣ ከኦህዴድም ጋር መሆኑን ልብ ማለት ያስፈልጋል።
ወልቃይት እስከ አሁን ድረስ በጀት በኦህዴድ ተከልክሏል። በምክትል ጠ/ር ሚኒስትር አህመድ ፋራ የመስክ ጥናትና ምክረ ሃሳብ መሰረት፣ የገንዘብ ሚኒስትሩ አህመድ ሸዴና የፌዴሬሽን ምክር ቤት ሰብሳቢ አገኘው ተሻገር ለወልቃይት በጀት እንዲለቀቅ ተፈቅዶ፣ በአብይ ቀጥተኛ ጣልቃ ገብነት ውሳኔው መቀልበሱን ኮ/ል ደመቀ ዘውዴ ነግረውናል።
ኮረምን፣ ራያን፣ ጠለምትን አብይ መከላከያ ለቆ እንዲወጣ አድርጎ ለወያኔ ማስረከቡና ወልቃይት ላይ ለሚያመጣው አንደምታ የአነ ኮ/ል ደመቀ ምላሽ፣ የተከዜን ዘብ በመከላከያ ድጋፍ ማንቃት፣ ማሰልጠን፣ ማደራጀትና ማስታጠቅ ሆኗል።
በእርግጥ የወልቃይት ውስብስብ ሁለገብ ትግል ያልገባቸው ሰዎች፣ ለምን የወልቃይት ኮሚቴዎች የአማራ ብልጽግናን በግልጽ ተቀላቀሉ፣ ለምን ከመከላከያ ጋር አብረው ይሰራሉ፣ ለምን ፋኖን በግልጽ አይደግፉም ሲሉ ይደመጣሉ።
ወልቃይት ያለው መከላከያ ወልቃይትን ከተከዜ ዘብ ጋር ሆኖ ከወያኔ እስከጠበቀ ድረስ፣ የተከዜ ዘብን እስካሰለጠነና እስካስታጠቀ ድረስ፣ ለምን ብለው ከመከላከያ ጋር ይጋጩ? ምን ለማግኘት?
የአብይ ኦህዴድ በአብይ ቀጥተኛ ትዕዛዝ ለወልቃይት በጀት አልለቅም ብሎ፣ በጀታቸውን ከኦህዴድ አማራ/ብአዴን እያገኙ እያለ፣ እንዴትና ለምን ብለው ከብአዴን ጋር ቅራኔ ውስጥ ይግቡ?
አሁን ላይ የተከዜ ዘብ ከፋኖ ጋር ቢቀላቀል እንኳን፣ አሁን ፋኖ ባለው ቁመና ወልቃይትን ከአብይና ወያኔ የጋራ ጥቃት ተቋቁሞ ለምን ያህል ጊዜ ማቆየት ይችላል? ታዲያ በእጃችን ይዘን ለማቆየት ለጊዜው አቅም ከሌለን፣ የተሻለ አማራጭ እስከምናመጣ ድረስ፣ የወልቃይት ኮሚቴ መንገድ እንዴት ስህተት ሊሆን ይችላል?
ከፕሪቶሪቶያ ስምምነት በተቃራኒ ትጥቅ ማስፈታቱን ትቶ ለወያኔ ሁለገብ እርዳታ መስጠት ቅድሚያ የሰጠው ኦህዴድ፣ እቅዱ ወያኔን አበረታቶ ወልቃይትንና አማራውን ወሮ ጦርነት በማስከፈት ስልጣኑን ካለስጋት ማስቀጠል ነበር። ሰሞኑን አንዳንድ የወያኔ ባለስልጣኖች የአብይ ኦህዴድን እቅድ ያከሸፍነው፣ ከአማራ ጋር መጣላት ስላልፈለጉ እንደሆነ እንደሚነግሩን ሳይሆን፣ በዋናነት ወያኔ በአብይ ምክር ያልገፋበት በጦርነቱ ሞራሉና ስነ ልቦናው ክፉኛ ስለተጎዳ፣ ዳግም ጦርነት ማሰብ የሚይችልበት የሽንፈት ስነልቦና ውስጥ ስለነበር ነበር።
አሁን ዋናው የወያኔ ፍንካች በኢሳያስ ተጠልፎ ስለተወሰደና አማራውን መውጋት እንደማይችል ሲረዳ፣ አብይ የወልቃይትን ጉዳይ የፍርድ ቤት ጉዳይ በማስመሰል ድራማውን ቀጥሏል።
አብይ ሳያዘው የፌዴሬሽን ምክር ቤቱ አገኘው ተሻገር፣ ለመጪው ምርጫ ወልቃይት፣ ራያና ኮረም ከትግራይ ባንቱስታን ውጪ ሆነው ምርጫ ይካሄድባቸዋል ብሎ ለምርጫ ቦርድ ትዕዛዝ ሊያስተላልፍ አይችልም። ፍርድ ቤትም የአብይ ይሁንታ ሳያገኝ የጌታቸው ረዳን እግድ ተግባራዊ አያደርግም። የፓለቲካ ሞቴን አልሞትኩም የሚለው አብን በጉዳዩ ጣልቃ መግባት እፈልጋለሁ ብሎ ለፍርድ ቤት አቤቱታ ማስገባቱ የአብይ ድራማ አካል ነው።
የወልቃይት ኮሚቴም እንደ ሁልጊዜው የፍርድ ቤቱን ጉዳይ እንደ ሰላማዊ ትግሉ አካል በመቁጠር ፣ የፍርድ ቤቱ ክርክሩ ውስጥ ለመግባት ፍቃድ እንዲሰጠው ማመልከቻ አስገብቷል። ኦህዴድንና ወያኔን በፍርድ ቤት ሰላምዊ ትግል ለመሞገት።
ወልቃይት በተከዜ ዘብ እጅ እስካለ ድረስ፣ የወልቃይት ኮሚቴን ውስብስብ ሁለገብ ትግል የተረዳ ፋኖ፣ ወደ ወልቃይት ከተከዜ ዘብ ጋር ውጊያ የሚከፍትበት አንዳችም አሳማኝ ምክንያት አይኖረውም። በእርግጥ ከታመነበት ራያን፣ ኮረምንና ጠለምትን አብይ ለወያኔ ለቆ ስለወጣ፣ የፋኖ አመራሮች ካመነቡትና ቅድሚያ የሚሰጠው ጉዳይ ነው ካሉ፣ ፋኖ እንዚህ አካባቢዎችን ከወያኔ ነጻ እንዲያወጣ ሊታገል ይችላል።
ካለጥርጥር የወልቃይት ኮሚቴ ከብአዴንና ከኦህዴድ ጋር የገባው ጋብቻ በእርግጠኝነት አማራጭ የሌለው እርምጃ ነው። ለጊዜው የተሻለ አማራጭ የለም። ኦህዴድም፣ ብአዴንም ይሄ አይጠፋቸውም።
ወልቃይት በእጃቸው እስካለች ድረስ፣ የወልቃይት ኮሚቴ ውስብስብ ሁለገብ ትግል ያለበትን ችግር እኛ የፋኖ ደጋፊዎች መረዳት ያስፈልገናል።
እነ ኮ/ል ደመቀ ዘውዱ የቁርጥ ቀን ሲመጣ ነው እውነተኛ አቋማቸው የሚታወቀው። ኮለኔል ደመቀ ወልቃይትን አሳልፎ ከሰጠ ያኔ እንወቅሰዋለን። የተከዜ ዘብም ይሄንን ግፍ ከተቀበለ እንጠይቀዋለን። እስከዛው ትግል ያማረው ወደ ራያና ጸለምት መትመም ይችላል። በግድ ጠገዴ እና ሁመራ ልግባ ማለቱ ኪሳራ እንጂ ትርፍ አያመጣም።
በፕሪቶሪያ ስምምነት መሰረት ወያኔን ትጥቅ ማስፈታት የሚገባው ኦህዴድ፣ ጭራሽ ወያኔን ከባድ መሳሪያውን ይዞ እንዲቀመጥ ስምምነት ላይ መደረሱን ሬድዋን ሁሴን ከናይሮቢ ስምምነት በኋላ ነግሮናል። ኦህዴድ ይሄ አላንስ ብሎት፣ የአማራ ልዩ ኃይልን ከፕሪቶሪያ ስምምነት ማግስት በቅድሚያ ሊያፈርስ ሲንቀሳቀስ፣ በአንድ ጀምበር ልዩ ኃይሉ የፋኖ የሰለጠነ እርሾ በመሆን፣ ለፋኖ በይፋ መመስረት ምክንያት እንደሆነ ቆም ብሎ ማሰብ ያስፈልጋል።
እነ ኮ/ል ደመቀ ከህዝብ ልብ መውጣት ያለባቸው፣ የቁርጥ ቀን መጥቶ፣ ወልቃይትን አብይ ለወያኔ አሳልፎ ሰጥቶ፣ ከአብይ ጋር ከሰሩ ነው።
እስከ አሁን ያለው ተሞክሯቸው እንደሚያሳየን፣ የወልቃይት ኮሚቴ በወልቃይት ጉዳይ ከማናቸውም ኢትዮጵያዊ በላይ ተፈናቅለዋል፣ ተሰቃይተዋል፣ ታስረዋል፣ ተገለዋል። ባጭሩ በወልቃይት ጉዳይ ብዙ ፍዳ አይተዋል፣ እያዩም ነው። እስከ አሁን ድረስ ትጥቅን ጨምሮ እየተጠናከሩ ከመሄድ ውጪ ሸብረክ ሲሉ አልታዩም።
የሰላማዊ ትግል ኣልፋና ኦሜጋን ምንነትን በቅጡ በመረዳት በጽናት አየታገሉ በተግባር እያሳዩን ነው።
ኢትዮጵያኖችና የአማራ ህልውና ደጋፊዎች ማወቅ ያለባቸው፣ የወልቃይት ኮሚቴ ትግል ውስብስብ ነው። ትግሉ ከአብይ ኦህዴድና ከተለያዩ የወያኔ ፍንካቾች ( ከደብረ ጽዮን…..እስከ ጌታቸው ረዳ) ጋር ነው።
የወልቃይት ኮሚቴን ለመከፋፈልና ለማዳከም፣ ኮሚቴው ከአማራው ህዝብ እንዲነጠል፣ ከኦህዴድና ከወያኔ ያልተቋረጠ የተቀነባበረ የስም ማጥፋት ዘመቻ ይካሄድባቸዋል። በተለይ ኮ/ል ደመቀ ዘውዱን ነጥሎ ለመምታት ኢትዮ ፎረምን ጨምሮ የማይሰራ ፕሮፓጋንዳ የለም። ይሄን ለምን ብለን መጠየቅ አለብን። በእርግጥ ለወልቃይት ህዝብ ተጨንቀው ይመስላችኋል? እየነጠሉ ለማጥፋትና በመጨረሻም ረግጦ ለመግዛት ነው።
በእርግጥ ኮ/ል ደመቀ ዘውዱ አክሊሉ ሃ/ወልድ፣ ከተማ ይፍሩ፣ አዲስ አለማየሁ፣….አይደሉም። እያወቁ ሸብረክ አይሉም ብንል እንኳን፣ ከጎናቸው ቆመን ሁለ ገብ ድጋፍ ካላደረግንላቸው፣ በኦህዴድና በወያኔ የተራቀቀ ሴራ ሊጠለፉ ይችላሉ።
ከሁሉም የከፋ ታሪክ ይቅር የማይለው ጥፋት የሚሆነው ደግሞ፣ እኛ የኦህዴድና የወያኔ ሴራ ሳይገባን፣ የወልቃይት ኮሚቴን ያልተለመደ አካሄድ በቅጡ ሳንረዳው፣ የተከዜን ዘብ ለመገዝገዝ ስንሰራ ነው። ግራ እጅን በቀኝ እጅ መቁረጥ ነው የሚሆነው።
Opinions expressed by contributors are their own. Ethiofact does not endorse and is not responsible for the accuracy of any of the views expressed in the content on this site.