“አወዛጋቢ ቦታዎች”፣ መጪው “ምርጫና የፍርድ ቤት” ጉዳይ

በአበራ ገ/ማርያም

ምንም እንኳን የኦህዴድና የሕወሃት የፕሪቶሪያ ስምምነት “አወዛጋቢ ቦታዎች” ባሉበት ማለትም በአማራ ክልል ባንቱስታን እጅ ቆይተው በህገ መንግስት/ ህገ ሕወሃት መሰረት የዘለቄታ መፍትሄ ይሰጣቸዋል ቢልም፣ ሲጀምር “አወዛጋቢ ቦታ” የሚባል ነገር የለም። የፕሪቶሪያ ስምምነት “አወዛጋቢ ቦታዎች” የሚላቸው ሕወሃት ከጻፈው የሽግግር መንግስት ቻርተርና ህዝቡ ላይ በኃይል ከጫነው ህገ መንግስት በፊት፤ ወልቃይትን ከጎንደር ራያን ከወሎ ክ/ሀገር በጠራራ ፀሃይ ወደ ትግራይ ክ/ሀገር በኢምፔሪያል ሕወሃት የተጠቃለሉ ናቸው።

እባብ የሆዱን አይቶ እግር ነሳው ሆኖ እንጂ፣ የሕወሃት “ታላቋ ትግራይ” ቅዠትማ አባይ ግድብን፣ ላሊበላን፣ ራስ ዳሽንን፣ አሰብን ፣….ይጠቀልላል።

ባጭሩ ወልቃይትና ራያ በኃይል የተወሰዱት ህገ መንግስቱና የሽግግር መንግስቱ ቻርተር “ከመጫናቸው” በፊት ሰለነበረ፣ መፍትሄው ለባለቤቱ ለጎንደርና ለወሎ ክ/ሀገሮች ካለምንም ማቅማማት መመለስ እንጂ፣ ችግሩ ከተፈጠረ በኋላ በተፈጠረው ህገ መንግስት/ህገ ህወሃት መሰረት እልባት ሊገኝላቸው አይችልም።

ምዕራብ ትግራይም ሽሬ እንጂ፣ አፍቃሪ ሕወሃቶች እንደሚያነበንቡት ወልቃይት እንዳልሆነ በተገኘው አጋጣሚ አስረግጦ መናገር ያስፈልጋል። ሃቅ ያንቃል እንዲሉ አፋቸውን ሞልተው ወልቃይት ብለው መጥራት እንኳን ድፍረቱና ወኔው የላቸውም። ልክ የሚዋሸ ሰው የሰው አይን እያየ መናገር እንደሚቸግረው።

፩. የኮ/ል ደመቀ ዘውዱ መንገድ:

የኮ/ል ደመቀ መንገድ ውስብስብ ነው። ዋናው ዓላማው ወልቃይትን በእጁ ይዞ፣ ለዘለቄታው ወልቃይትን ወደ ጎንደር ለመመለስ ሁለገብ ትግል ማድረግ ነው።

በአብይና በመከላከያ እርዳታ የተከዜ ዘብ እየነቃ፣ እየተደራጀ፣ እየሰለጠነ፣ እየታጠቀ ነው። ከሱዳንም ይሁን ከምዕራብ ትግራይ ተከዜን አቋርጦ የሚመጣን ማናቸውም የወያኔን ጦር ወደ ወልቃይት ዝር እንዳይል እየተከላከለ ነው።

የወልቃይት ኮሚቴ በጀት በአብይ ቢከለከልም፣ ከብአዴን በሚያገኘው ድጎማ፣ የወልቃይት ህዝብ እራሱን በራሱ እያስተዳደረ ይገኛል። ኮ/ል ደመቀ አንድ ወቅት ማንነት በበጀት አይለወጥም በማለት ለኦህዴድ ቁርጡን ተናግሯል።

ወልቃይትን በእጁ ይዞ፣ አማራጭ ከማጣት ላይ ላዩን ሲታይ የአብይ ወዳጅ ቢመስልም፣ የወልቃይት ኮሚቴ ከጌታቸው ረዳና ከአብይ ኦህዴድ ጋር ውስብስብ የሰላማዊ ትግል ውስጥ ይገኛል።

የተከዜ ዘብንና ፋኖን ማጋጨት፣

የወልቃይት ኮሚቴ ላይ አልቡላታ መንዛት፣ ኮ/ል ደመቀን ከአማራ ህዝብ ጋር ማጋጨት፣ ……የአብይና የጌታቸው ረዳ ዋናው ስትራተጂ ነው።

አሁን ደግሞ ጌታቸው ረዳ የምርጫ ቦርድ ውሳኔን በፍርድ ቤት የማሳገዱን ክርክር በጠበቃው በኩል አቋርጬያለሁ ብሏል። የወልቃይት ኮሚቴ ለፍርድ ቤቱ ይሄን ውሳኔ ከጌታቸው ረዳ ጠበቃ በተጨማሪ የራሱ ጌታቸው ረዳ አቋም መሆኑን ለፍርድ ቤቱ እንዲያሳውቅ፣ ከዚህ በኋላ ይሄን ጉዳይ ዳግም ፍርድ ቤት በማናቸውም ጊዜ ይዞት እንደማይመጣ ለፍርድ ቤቱ እንዲያሳውቅና፣ ለወልቃይት ኮሚቴ ጉዳዩን ለመከታተል ለጠበቃ ያወጣውን ወጪ እንዲክስ ለፍርድ ቤቱ ጠይቋል።

የወልቃይት ኮሚቴ ምርጫ ውስጥ ለመሳተፍ እየተዘጋጀ ነው። ከምርጫ ተሳትፎ በኋላ አብይ በጀት አልለቅም የሚልበት ሰበብ ይታያል። ኮሚቴው በጀት በቀጥታ ካገኘ፣ ከብአዴን ቀጥታ ተጽዕኖ ነጻ ይወጣል። ከምርጫው በኋላ ጌታቸው ረዳም ሆነ ማናቸውም የወያኔ ስንጣቂ የወልቃይት አስተዳደር ይፍረስ ማለት ቀላል አይሆንላቸውም። በህዝብ የተመረጠ አስተዳደር ስለሚሆን።

በአንድ እጁ ጠመንጃ በተከዜ ዘብ አማካኝነት ወልቃይትን ከወረራ በደሙ እየተከላከለ፣ በሌላ እጁ ለየት ያለ ያልተለመደ ሰላማዊ ትግል (በመከላከያ እርዳታ የተከዜ ዘብን ማሰልጠንና ማስታጠቅ፣ የፍርድ ቤት ሙግት፣ በምርጫ መሳተፍ፣ ወልቃይትን ማስተዳደር፣ የአብይን ወጥመድ ወዳጅ መስሎ በቅርብ እየተከታተሉ ማክሸፍ፣ …..) እያካሄደ ነው።

የወልቃይት ኮሚቴ ያልተለመደ አካሄድ ከአብይ ኦህዴድና ከብአዴን ጋር በቅርብ መስራታቸው፣ የተወሰነ የህብረተሰብ ክፍልን እያሳሰበ፣ ያስጨነቀ፣ እያሳዘነ ይገኛል። ይሄ የሚጠበቅ ነው።

ወልቃይትን በእጃቸው ይዘው እስካስተዳደሩ ድረስ፣ የወልቃይት ኮሚቴ ከአብይ፣ ከኦህዴድ፣ ከብአዴንና ከመከላከያ ጋር የመጋጨት ፍላጎት እንደሌላቸው ግልጽ ነው።

ነገር ግን ወልቃይትን አብይ ለወያኔ አሳልፎ የሰጠ ቀን፣ የወልቃይት ኮሚቴ አብሮ ከአብይ ጋር መስራት ከቀጠለ፣ ያኔ ሁሉም ነገር ይቀየራል። የወልቃይት ኮሚቴ ካለፈ ታሪኩ በመነሳት በቀላሉ ለማንም በወልቃይት ጉዳይ ሸብረክ ይላል ማለት ከባድ ነው።

፪. የአብይ መንገድ

ከወያኔ ውድቀት በኋላ የስልጣን ባላንጣዬ አማራው ነው ብሎ ኦህዴድ ስለደመደመ፣ የፕሪቶሪያ ስምምነት ላይ ፋኖና ኢሳያስን አግልሏል። ወያኔን ደግሞ ከሬሳ ሳጥን ውስጥ ጎትቶ አውጥቶ፣ ነፍስ ዘርቶበታል።

የፕሪቶሪያ ስምምነቱ ሕወሃት ሙሉ ለሙሉ ትጥቅ ይፈታል ቢልም፣ በናይሮቢ ስምምነቱ ከባድ መሳሪያ ሳይቀር ይዘው እንዲቀመጡ ብርሃኑ ጁላ፣ ሬድዋን ሁሴንና ጌታቸው ረዳ ተስማምተዋል። ይሄ የአብይ ክህደት፣ ከፋኖና ከኢሳያስ ጋር እንዲቆራረጥ አደረገው።

አሁን የወያኔ አንዱ ፍንካች የሞንጆሪኖ ቡድን ከአብይ ጋር የማይታረቅ ቅራኔ ውስጥ ሲገባ ሴራውን ግልጽ አድርጎታል። በፕሪቶርያ ስምምነት ማግስት አብይ በድብቅ የኦህዴድ ተወካይ ሱዳን ድረስ ልኳል። ወልቃይትን ሊወር በተደጋጋሚ ሞክሮ ያልተሳካለትን ሱዳን የነበረውን የወያኔ አርሚ 70 እንዳይበተን ብዙ ሚሊዮን ዶላር ሰጥቶ ካምፕ ውስጥ እንዲቆይ አድርጓል።

ይሄ የአብይ መሰሪ ሴራ በጊዜው የወያኔ መሪዎች ሳይቀር ግራ አጋብቷቸው ነበር። ትግራይ በየካምፑ ውስጥ ያስቀመጣቸው የወያኔ ታጣቂዎች ደግሞ፣ አብይ በትግራይ ጊዝያዊ አስተዳደር በኩል ቢሊዮኖች እየላከ እየተቀለቡ ለክፉ ቀን እንዲቀመጡ አደረገ።

ጎን ለጎን ኦህዴድ በፕሪቶሪያ ስምምነት ማግስት የአማራ ልዩ ኃይልን ነጥሎ አፍርሶ ለፋኖ በፍጥነት መፈጠር ዋና ገፊ ምክንያት ሆነ።

ሱዳን ያለው አርሚ 70ን ከመበተን ያዳነውና፣ ትግራይ ያለው ካምፕ ገብቶ እንዲቀለብ የተደረገው የወያኔ ሰራዊት አብይ ወልቃይትን ገፋፍቶ እንዲወሩ በማድረግ፣ የአማራና የትግራይ ህዝብን የማያቋርጥ ጦርነት ውስጥ ለመክተት ነበር። የዛሬን አያድርገውና ወያኔ ናፋቂ ጋዜጠኛ ዳዊት
ከበደ በኦፊሻል የፌስቡክ ገጹ ሳይቀር፣ ከኦህዴድ ጋር ተባብረን ወልቃይትን ወረን በመውሰድ አማራን እንበቀል ብሎ የአብይን ፍላጎት ደግሞ ደጋግሞ በማስተጋባት ይጽፍ ነበር።

ይሄን የአብይን ሴራ የእንግዴ ልጁ ብአዴን እንዳይጠረጥር ፣ አገኘው ተሻገርን የፌዴሬሽን ምክር ቤት ሰብሳቢ አደረገው። ምናልባትም ብአዴን እንዳይጠረጥር የፌዴሬሽን ምክር ቤት ኃላፊ መሆናችው የወልቃይትን እጣ ፋንታ እንዲወስኑ አብይ ፍላጎቱ እንደሆነ ቃል ገብቶላቸው ይሆናል ። ለነገሩ ብአዴን ማሰብ የማይችሉ ፍጡሮች ስብስብ ሆኖ ነው እንጂ፣ የፌዴሬሽን ምክር ቤትን በበላይነት መቆጣጠሩ ብዙ እድሎችን ይዞለት መጥቷል።
ወያኔ በጦርነቱ በደረሰበት ከፍተኛ የሞራል ስብራትና የስነ ልቦና ሽንፈት ማገገም ስላልቻለ፣ አብይን እንደ ፌዴራል መንግስትነትህ ወልቃይትን አስለቅቀህ ስጠኝ እንጂ፣ አልዋጋም ብሎ ተማጸነ። ከዛሬ ነገ ወያኔ ሃሳቡን ይለውጣል ብሎ አብይ ሲጠብቅ፣ ወያኔ እንደ አባ ጨጓሬ እየተፈነካከተ እየተሰነጣጠቀ ከትግራይ ህዝብ ልብ ውስጥ እየወጣ እራሱን ከጨዋታ ውጪ እያደረገ መሄድ ጀመረ። ጭራሹንም ማፈግፈጊያ ሜዳ ፍለጋ የሞንጆሪኖ የወያኔ ፍንካች፣ ኢሳያስ ጉያ ስር ሄዶ በመሸጎጥ የአብይ ቀንደኛ ጠላት ሆነ።

አብይ አርሚ 70 ትጥቅ መፍታት (DDR) ጀምረዋል ብሎ ሰሞኑን መግለጫ አውጥቶ፣ የወያኔው ጄኔራል ታደሰ ወረደን እጣ ፈንታ በሚወስን መልኩ፣ የሞንጆሪኖ ቡድን የሕወሃት ጄኔራል ማንጁስ አብይን በቀጥታ የሚሰድብና የሚያጥላላ መግለጫ በጊዚያዊ አስተዳደሩ የፀጥታ ቢሮ ስም ግብረ መልስ ሰጥቷል።

ለወያኔ ሰራዊት በጀት መድቦ ካምፕ ማቆየት ከአሁን በላይ ጉዳቱ እንጂ ጥቅም እንደሌለው የተረዳው አብይ፣ የወልቃይትን የፍርድ ቤት ካርድ መዞ ብቅ ብሏል። “አወዛጋቢ ቦታዎች” ከትግራይ ባንቱስታን ክልል ውጪ ሆነው ምርጫ ያካሂዳሉ ብሎ በአገኘው ተሻገር ለምርጫ ቦርድ እንዲጻፍ አብይ አደረገ። ጌታቸው ረዳ በፍርድ ቤት ይሄን ውሳኔ አሳገደ፣ የወልቃይት ኮሚቴና አብን ጉዳዩ ስለሚያገባን፣ ክርክሩ ላይ መሳተፍ እንዲፈቀድላቸው ለፍርድ ቤት ጠየቁ።

ታንኩና ባንኩን ሕወሃት እስከልተቆጣጠረ ድረስ፣ የመለስ ዜናዊ የፌዴሬሽን ቀመር ትግራይን እንደሚጎዳ ጌታቸው ሲገባው ፣ የፍርድ ቤት እግዱን ትቼዋለሁ፣ የፓለቲካ ውሳኔ ይሰጠን ብሎ ለአብይ ሴራ ምቹ ሁኔታ አመቻችቷል።

አንድ አስረግጦ መሰመር ያለበት ነገር ቢኖር፣ የፌዴሬሽን ምክር ቤቱ አገኘው ተሻገርም፣ ፍርድ ቤትም፣ አብንም ሆነ የጌታቸው ረዳ ስምረት ከአብይ ፍላጎት ውጪ እንደማይንቀሳቀሱ ግልጽ ነው።

፫. የጌታቸው ረዳ መንገድ

የጌታቸው ቡድን በአብይ እርዳታ ወያኔን አስወግደን ትግራይን መልሰን መቆጣጠር እንችላለን ብሎ ያምናል። ጌታቸው ነገርን ረጋ ብሎ በቅጡ ማየት የማይችል ሰው ነው።

ጌታቸው ከአብይ ጋር መስራቱ ከትግራይ ህዝብ ልብ ውስጥ እንዲወጣ አድርጎታል። የአብይ የምስራቅ አፍሪካ አማካሪ ሆኖ ጌታቸው ሲሾም የፓለቲካ ሞቱን ሞቷል። ከትግራይ ጋር ያለውን ትስስር በጥሶታል።

የጊዜ ጉዳይ ነው እንጂ አብይ ጌታቸው ላይ የቋጠረውን ቂም አይረሳም። ጌታቸው ለአብይ የሚሰጠው ጥቅም ሲያበቃ ካለጥርጥር ይበቀለዋል። እስከዚያው ጌታቸው የአብይን ቆሻሻ ስራ ትግራይ ውስጥ ይሰራል። አብይን ተገን አድርጎ፣ ጌታቸው የግል ቂሙን ህይወቴን ሊያጠፉት ነበር ብሎ የወነጀላቸውን ሕወሃትን ይበቀላል።

ጌታቸው ከትግራይ ህዝብ ጋር ያስታርቀኛል ብሎ ያሰበው አጀንዳ ወልቃይት ብቻ ነው። ስለ ወልቃይት፣ ስለ ወልቃይት እስተዳደር፣….እርስ በእርሱ የሚጣረስ መግለጫዎች በተለያየ ጊዜ በመስጠት ውዥንብር እየነዛ ይገኛል።

እነ ኮ/ል ደመቀ ላይ ነጋ ጠባ ውዥንብር ይነዛል፣ የወልቃይት አስተዳደሩ ይፈርሳል ማለት ከጀምረ ዓመታት አልፈውታል፣ …..። የእነ ኮ/ል ደመቀ መልስ ደግሞ የሚጠናከር እንጂ የሚፈርስ አስተዳደር የለም ነው።

አሁን ደግሞ ምርጫ ቦርድ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ትዕዛዝ መሰረት አድርጎ፣ “አወዛጋቢ ቦታዎች” ከትግራይ የአፓርታይድ ባንቱስታን ክልል ውጪ ሆነው ምርጫ ይካሄድባቸዋል ብሎ መወሰኑን ተቃውሞ፣ የፍርድ ቤት እግድ ጠይቆ ተፈቅዶለት ነበር።

ከቀናቶች በኋላ ጌታቸው ረዳ የፍርድ ቤት እገዳ ክርክሩን በጠበቃው በኩል ማቋረጡን ተናግሯል። ምክንያቱ ደግሞ ሲያብራራ ውሳኔውን የወሰነው ፌዴሬሽን ምክር ቤት እንደ ተቋም ሳይሆን፣ በግለሰቦች ደረጃ ስለሆነ፣ የፍርድ ቤት ጉዳይ ሳይሆን የፓለቲካ መፍትሄ ነው የሚያስፈልገው ብሏል።

መለስ ባንኩና ታንኩ ሁሌም በሕወሃት እጅ ይሆናል ብሎ አስልቶ፣ በአፓርታይድ ባንቱስታን ክልሎች መካከል የሚነሱ ውዝግቦች፣ የመጨረሻ ውሳኔ ሰጪ ይብዛም ይነስም ህግ ከተማሩት የፍርድ ቤት ዳኞች ይልቅ ሕወሃት በሚቆጣጠረው በሕወሃቷ ኪሪያ ኢብራሂም የሚመራውን የፌዴሬሽን ምክር ቤት እንዲሆን በህገ መንግስት ደንግጓል።

ጌታቸው ረዳ እንደ ህግ እንዳጠና ሰው፣ ፍርድ ቤት ነገሩን ከማምጣቱ በፊት ይሄን ሩቅ አሳቢ ቅርብ አዳሪ የመለስ ሴራ ሊገባው ይገባ ነበር። መለስ የመጨረሻውን የውሳኔ ስልጣን በህገ መንግስት የሰጠው ለፍርድ ቤት ሳይሆን ለፌዴሬሽን ምክር ቤት ነው።

በዚህ የተነሳ ጌታቸው የፍርድ ቤት ድራማውን ትቶ ኳሱን ወደ አብይ መልሶ ወርውሯታል፣ የፓለቲካ ውሳኔ ይሰጥ ብሎ። ጌታቸው ረዳ የወልቃይት ካርድ ከእጁ ከወጣበት በትግራይ ፓለቲካ ውስጥ መሉ ለሙሉ ከጨዋታ ውጪ እንደሚሆን፣ የአብይን ቆሻሻ ስራ መስራት እንደማይችልና ጌታቸውም ህወሃትን መበቀል እንደማይችል፣ ለአብይም ለጌታቸውም ግልጽ ነው። ለጊዜው አብይና ጌታቸው ይፈላለጋሉ።


Opinions expressed by contributors are their own. Ethiofact does not endorse and is not responsible for the accuracy of any of the views expressed in the content on this site.

guest

0 Comments
Oldest
Newest Most Voted
Inline Feedbacks
View all comments

0
Would love your thoughts, please comment.x
()
x