Fano Elite Force
የፋኖ ኮማንዶ ምረቃ ስነስርአት

የፋኖ ትግል የህልውና ወይስ ብሔረተኝነት?

በአበራ ገ/ማርያም

በአሁኑ ወቅት አንዳንድ ሰዎች የፋኖን ትግል የአማራ ብሄረተኝነት ትግል አድርገው ሲያቀርቡት፣ የተወሰኑ ሰዎች ደግሞ ከብሔርተኝነት የተለየ የህልውና ትግል አድርገው ይስሉታል።

ከዚህ በታች የፋኖ ትግል እንዴት ከሻዕቢያ፣ ከወያኔ፣ ከኦነግ አግላይና አውዳሚ የብሄር ፓለቲካ እንደሚለይ ለማሳየት እሞክራለሁ።

፩. የብሄር ድርጅቶች የተፈጠሩበት ምክንያት

የተለያዩ ፍላጎት ባላቸው ምዕራብያውያንና የአረብ አገሮች ቆስቋሽነት፣ በጀብኃ የተጀመረውና በሻዕቢያ ኤርትራን በመገንጠል ለጊዜውም ቢሆን የተጠናቀቀው የኤርትራ ብሄረተኝነት ዋና መነሻው ምክንያት ፌዴሬሽኑ ከኤርትራ ህዝብ ፍላጎት ውጪ ፈረሰ፣ በኤርትራ የብዙሃን ፓርቲ ስርዓት ተቋረጠ፣ የግል ሚዲያ ታገደ፣…የሚል ነበር። ከዚህ ቅሬታ ውጪ ኢትዮጵያ ውስጥ ከነበሩት 14 ክፍለ ሀገሮች፣ የኤርትራ ተወላጆችን ያህል በኢትዮጵያ ውስጥ የትምህርት እድል ያገኘ፣ ሀብት ያካበተ፣ የመንግስት ሹመኛ የሆነ፣ …የአንዳችም ክፍለ ሀገር ተወላጅ አልነበረም። ለኤርትራ ክ/ሀገር የተደረገው የትምህርት፣ የጤና፣ የኢንዱስትሪ፣…ኢንቨስትመንት፣ ለሁሉም ክፍለ ሀገሮች ከተደረገው በእጅጉ ይበልጣል።

ዛሬ በኤርትራ “ከነጻነት” በኋላ አንዳቸውንም ታገልንለነት የሚሉትን እንኳን ሊያሳኩ ይቅርና፣ ወደባሰ አዘቅት ውስጥ ገብተው፣ ሰፊው የኢትዮጵያ እንጀራና ፀጋ እየናፈቃቸው፣ ደማቸው ደመከልብ ሆኖ ቀርቷል። የወያኔ ብሄርተኞች ሳይቀሩ “ኤርትራን ያየህ ተቀጣ” ብለው፣ የመገንጠል ሃሳባቸውን ከማስፈራሪያነት ውጪ ከምር እንዳይወስዱት ተጨማሪ ምክንያት ሆኗቸዋል።

በወያኔ መስራቾቹ አረጋዊ በርሄና ግደይ ዘራጽዮን በመጽሃፋቸው እንደተገለጹት፣ የወያኔ የትግራይ ብሄረተኝነት ዋና መነሻ ንግስናችን በሸዋ ተወሰደ፣ ትግራይ ውስጥ ፋብሪካ የለም፣ አድዋ ጦርነት ላይ የተሰዉ ኢትዮጵያኖችን የሚገባውን ክብር መስጠት ቀርቶ፣ የትግራይን የእህል ዘር ከጎተራ አውጥተው በተንኮል በልተው ትግራይን ደሃና ለማኝ አድርገው አስቀሩ፣ ትግራይ ውስጥ በትግርኛ መማር አንችልም፣ ……. ነበር።

ትግራይ ደርግ ወደ ስልጣን እስኪመጣ ድረስ፣ ከሌሎቹ ክፍለ ሀገር በተለየ ሁኔታ አንድም ቀን ከትግራይ ሰው ውጪ ተዳድራ አታውቅም። የኢኮኖሚ፣ የትምህርት፣.. ….ተጠቃሚ ለመሆን የህዝብ ፍልሰቱም ከትግራይ ወደ ቀረው የኢትዮጵያ ክፍል እንጂ ፣ ወደ ትግራይ አይደለም። በግምት ከ1. 5 ሚሊዮን የትግራይ ህዝብ በተቀረው ኢትዮጵያ ሲኖር፣ ከድምበር ጠባቂ ወታደር ውጪ ይሄ ነው የሚባል የትግራይ ተወላጅ ያልሆነ ኢትዮጵያዊ በትግራይ አይኖርም። በአጎረስኩኝ እጄን ተነከስኩኝ ሆነና፣ በመላ ኢትዮጵያ በሰላም ተዘዋውረው እንዲነግዱና እንዲበለጽጉ ላደረገች ኢትዮጵያ፣ የትግራይ ብሄረተኞች መልስ የወርቅ እንቁላል የምትጥለውን እንቁላል ገድሎ፣ ወደ መቀሌ ወደ ጭለማ መመሸግ ሆነ።

በኦሮሙማ አራማጆች የሚቀነቀነው የኦሮሞ ብሄረተኞች ትርክት ሙሉ ለሙሉ በውሸት ላይ የቆመ ነው። ሻዕቢያና ወያኔ የራሳቸውን ዓላማ ለማሳካት የኦሮሙማን ብሄረተኝነት ተጠቅመውበታል። ሲጀምር የሜጫና ቱለማ እንቅስቃሴ በሸዋ ( የአማራና የኦሮሞ) ተወላጆች የተጀመረ የሸዋ የስልጣን ይገባኛል ጥያቄ እንጂ፣ የኦሮሞ ብሄርተኝነት ጥያቄ አልነበረም። የኦሮሞ ጥያቄ የቀኝ ግዛት ጥያቄ ነው የሚለውም የትም የማያስኬድ የሀሰት ትርክት ነው። የእነ ተስፋዬ ገብረአብ አይነቱ የወያኔና የሻዕቢያ ወኪል የቡርቃ ዝምታ የሚል ተረት ተረት ጨምረውበታል። የአኖሌ ሃውልም የዚሁ የፈጠራ ትርክት ውጤት ነው።

የሻዕቢያም፣ የወያኔም፣ የኦሮሙማም ብሄርተኝነት በቋንቋችን አልተማርንም፣ አልተዳኘንም ከማለት ውጪ ምንም ሌላ ውሃ የሚቋጥር ምክንያት ማቅረብ አይችሉም።

ወደ አማራው ሲመጣ ግን፣ አማራውን በእቅድ ያገለለ፣ የሚያሳድድ፣ አገር አልባ ያደረገ የአፓርታይድ ስርዓት ተቀርጿል። አማራውን ለይተው. ጨቋኝ የሚል ታፔላ ለጥፈውበት ባለፈው 50 ዓመት አፈናቅለዋል፣ ገለዋል፣ አሳደዋል። በአሶሳ ሻዕቢያና ኦነግ አማራውን አዳራሽ ዘግተው በእሳት ለኩሰዋል። በበደኖ፣ በአርባጉጉ፣….ኦነግና ኦህዴድ አማራውን ከገደል ወርውረዋል፣ አርደዋል። ሌንጮ ለታ ይሄን ጭፍጨፋ በምክር ቤት ሳይቀር አምኗል። ወያኔ በተለይ በወልቃይት አማራ ላይ የዘር ማጥፋት ወንጀል ለ27 ዓመት ፈጽሟል።

በቅርቡ በኦሮሙማ አራማጆች አማራው በሻሸመኔ፣ በወለጋ፣ በመተከል፣ በጉራፈርዳ፣ …..ቤት ተዘግቶበት በእሳት ተቃጥሏል፣ እርጉዝ ሆዷን በሳንጃ ቀደው ገድለዋል፣ ደካማ አዛውንቶችን ሴቶችንና ህጻናቶችን ሳይቀር ያለርህራሄ አማራ ስለሆኑ ብቻ ጨፍጭፈዋል። ሕጻናቶች ወላሂ ሁለተኛ አማራ አልሆንም እስኪሉ ድረስ ታርደዋል።

ይሄ እንደ ቡርቃ ዝምታና አኖሌ ሃውልት የውሸት ትርክት ሳይሆን፣ ግፉ በቪድዮ ሳይቀር ተቀርጾ ተሰንዶ ከትውልድ ወደ ትውልድ ለማስተማርያነት ይተላለፋል። ለፍርድ ቀንም ተቀምጧል።

በጣልያን ወረራም ጊዜ አማራው ተለይቶ ተሳዷል፣ ተፈናቅሏል፣ ተገድሏል፣ ተሰቃይቷል፣….።

ከአማራ ውጪ እቤቱ ቁጭ ብሎ መንግስት ላይ ተቃውሞ ሳያነሳ፣ ሳያምጽ አንድም ብሄረሰብ በጎሳው ምክንያት የተፈናቀለ፣ የተገደለ፣ የተሳደደ፣….የለም።

ለዚህም ነው የአማራ ትግል የህልውና፣ የሞት ሽረት፣ የመኖር ወይም የመጥፋት ትግል የሆነው። የአማራ የህልውና ትግል ወርዶ ወርዶ እንደ ሻዕቢያ፣ ወያኔና ኦነግ ተራ የብሄረተኝነት ትግል ሊባል አይገባም። ልዩነቱ እናቱ ገበያ የወጣችበትና የሞተችበት ልጅ እኩል እንደማልቀስ ያህል ነው።

የሻዕቢያ፣ የወያኔና የኦነግ ብሄረተኝነት አንድ ላይ ተደምረው እንኳን አማራው ላይ የደረሰበትን ኢምነት ግፍ እንኳን አልደረሰባቸውም። ስለዚህ የአማራ ትግል የሞት ሽረት የህልውና ትግል እንጂ በፍጹም የብሄረተኝነት ትግል ብለን መጥራት የለብንም። የአማራን የህልውና ትግል አሳንሶ የብሄረተኝነት ትግል አድርጎ መናገር፣ በአማራው ቁስል ላይ እንጨጨት መስደድ ነው የሚሆነው።

፪. ህዝብን ወይስ ድርጅትን እንደ ጠላት?

የሻዕቢያ፣ የወያኔ፣ የኦነግ፣ የአህመድ ጀበል ውሃቢዝም አማራን እንደ ህዝብ ምንም ልዩነት ሳያደርጉ በጠላትነት ፈርጀው የሚገድሉት፣ የሚያሳድዱት፣ የሚያፈናቅሉት፣ ….።

ድርጅቶቹ በፓለቲካ ፕሮግራማቸው፣ በትግል ዘፈናቸው፣ በመግለጫቸው፣ በድራማቸው፣ በመጽሃፎቻቸው፣ …..የአማራን ህዝብ በግልጽ በጠላትነት ይፈርጃሉ፣ የጥቃት ሰለባ እንዲሆን ይቀሰቅሳሉ።

በወያኔ መሃንዲስነት የአርባ ጉጉንና የበደኖን እልቂት፣ አሁን በኦሮሙማ አበረታችነት የሚካሄደውን የወለጋን፣ የአርሲንና የመተከልን እልቂት፣ ….ማየት በቂ ነው።

ለአህመድ ጀበል ውሃቢዝም ህጻኗ አይሻ ሙስሊም መሆኗ ወይም “ወላሂ ሁለተኛ አማራ አልሆንም” ተማጽኖዋ፣ ከጥቃት አላዳናትም። ለአህመድ ጀበል ውሃቢዝም የአይሻ ጥፋቷ አማራ ሆና መፈጠሯ ነው።

ከጣልያን ወረራ በኋላ፣ በተደራጀና በተቀናጀ መልኩ የአማራ ህዝብ የጅምላ ፍጅት የጀመረው በሻዕቢያ ነው። በደርግ ዘመን በሻዕቢያ መሪነት፣ በወያኔና በኦነግ እርድታ፣ በያኔው የወለጋ ክ/ሀገር አሶሳ ውስጥ፣ አማራውን መርጠው አንድ አዳራሽ ውስጥ ሰብስበው በእሳት አጋይተው ጨርሰዋል። የሻዕቢያና የጁብሃ ትግል አልፋና ኦሜጋዎች የአማራን ህዝብ በጅምላ ጠላት አድርጎ መፈረጅ ነው። ዘፈናቸውን፣ ድራማቸውን፣ …. ማየት በቂ ነው።
በማህበራዊ ድህረ ገጽ ላይ አንድ አሮጊት በወያኔ በጫካ ዘመን “ይሄን አማራ በለው” የሚል ዘፈን ሲዘፍኑ በስፋት ተዘዋውሯል። በቅርቡ የወያኔ ጦርነት አንዷ የወያኔ ዘፋኝ በትግርኛ ” ይሄን አማራ ሁለተኛ አይለምደኝም፣ ውሃ ውሃ አስብለው” እያለች ስትዘፍን ትደመጣለች።

ኦነግና ወያኔ ያውም በውሸት ትርክት የአኖሌን ሀውልት አቁመው አማራውን ለእልቂት እንደዳረጉት ግልጽ ነው። የኦሮሙማ ሰዎች አማራውን ሳትመርጡ ግደሉ፣ ጨፍጭፉ፣ ብለው የለቀቋቸው የቪድዮና የድምጽ መረጃዎች ጊዜው ሲመጣ ፍርድ ቤት መቅረባቸው አይቀርም።

በተቃራኒ በፋኖ በኩል ግን አንድም ቦታ ወያኔን እንጂ የትግራይ ህዝብን፣ ሻዕቢያን እንጂ የኤርትራ ህዝብን፣ ኦሮሙማን እንጂ የኦሮሞ ህዝብን፣ የአህመድ ጀበል ውሃቢዝምን እንጂ እስልምናን እንደ ጠላት ፈርጆ አያውቅም።

ይሄ ህዝብና ድርጅትን የመለየት አካሄድ፣ የፋኖ ትግልን የህልውና እንጂ ጭፍን በጥላቻ የተሞላ የብሄርተኛ ትግል አያደርገውም።

ባጭሩ ብሄረተኝነት ሁሌም ጠላት ይፈልጋል።ለኤርትራ፣ ለኦሮሞና ለትግራይ ብሄረተኞች ጠላት ተደርጎ በፓለቲካ ፕሮግራም ሳይቀር የሰፈረው የአማራ ህዝብ ነው። የፋኖ ትግል ግን ጠላቴ ነው የሚለው አንድም ህዝብ የለም።

፫. ኢትዮጵያዊነት ወይስ ብሄረተኝነት?

የሻዕቢያ፣ የወያኔ፣ የኦነግ፣….ትግል “የነጻ አውጪነት” ትግል ነው። ስማቸው እንደሚገልጸው “ነጻ” የሚያወጡት ጎሳ አለ። ወያኔ አሁን ድረስ የትግራይ ህዝብ “ነጻ አውጪ” ድርጅት ነው። ሁሉም ነጻ እንወጣለን የሚሉት ደግሞ ከአማራው “ቀኝ አገዛዝ” ነው።

ነጻ አውጪ ጎሰኞቹ የራሳቸው ባንዲራ፣ የአፓርታይድ ባንቱስታን/ክልል፣ የራሳቸው የፈጠራ ታሪክ፣ ….አላቸው። የኢትዮጵያን ታሪክ ይጠየፋሉ፣ የኢትዮጵያን ሀገረ መንግስት ለማዳከም ቀን ከለሊት ይሰራሉ። ፋኖ ብአዴን የፈጠረውን የአማራ ባንቱስታን/ክልልና ባንዲራ አይቀበልም። የብአዴን ባንዲራ ምን እንኳን እንደሚመስል ፋኖም፣ የአማራ ህዝብም እንዲሁም የተቀረው ኢትዮጵያዊ አያውቅም።

ፋኖ ሰንደቅ ዓላማው የኢትዮጵያ እንጂ የተለየ የራሱ የለውም፣ ፋኖ በኢትዮጵያዊነቱና በኢትዮጵያ ታሪክ አይደራደርም፣ ፋኖ በኢትዮጵያ የዘለቄታ ብሄራዊ ጥቅም ላይ የጸና አቋም አለው፣

እነዚህ መገለጫዎች የፋኖን ትግል የጭፍን ብሄረተኝነት ሳይሆን የህብረ ብሄራዊ ተኮር የህልውና ትግል ያደርጉታል።

፬. ኢትዮጵያዊነት V ነጻ አውጪነት

ኦነግና ወያኔ አሁን ድረስ የነጻ አውጪ ስማቸውን አልለወጡትም። ኦሮሙማ ላለፈው 8 ዓመት፣ የወያኔ ለ27 ዓመት የመንግስት በትረ ስልጣን መጨበጣቸው ከመንደርተኝነት አላወጣቸውም።

የአማራ ህልውና ትግል የተጀመረው በፕሮፌሰር አስራት ወልደየስ በሚመራው በመዓህድ (በመላው ዓማራ ህዝብ ድርጅት ነው)። ጊዜው ሲደርስ በጥቂት ዓመታት ውስጥ መዓህድ በኢንጂነር ሃይሉ ሻወል መሪነት ወደ መኢአድ (መላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት) ካለምንም ግርግርና ተቃውሞ ተለውጧል። ከጎሳ ፓለቲካ ወደ ህብረ ብሄራዊ ፓለቲካ የተለወጠ ሌላ የጎሳ ፓርቲ ካለ ለመማር ዝግጁ ነን።

ጋሽ ታዲዮስ ታንቱ የወላይታ ተወላጅ ናቸው። ነገር ግን የመዓህድ አባልና አመራር ነበሩ። አቶ በድሩ አደም የኦሮሞ ተወላጅ ናቸው፣ ነገር ግን የመዓህድ የምርጫ ተወዳዳሪ ነበሩ። ብዙ በመርካቶ አካባቢ የሚኖሩ የጉራጌ ተወላጆች የመዓህድ አባል ሆነው ይሳተፉ ነበር። የኢትዮጵያ ወይም ሞት አባል የነበሩት ኤርትራዊው በላይ ተክሉ ለመዓህድ ዳጎስ ያለ የገንዘብ እርዳታ በቋሚነት ያደርጉ ነበር። ከተለያዩ ብሄር የተገኙ ኢትዮጵያኖች ለመዓህድ በተለየ ሁኔታ የእኔም ድርጅት ነው ብለው ድጋፍ የሚያደርጉት ኦነግና ወያኔ ከመሳሰሉ “ከነጻ አውጪ” ድርጅቶች እንደሚለዩ በመገንዘብ ነው።

የፋኖን ትግል ከጠባብ ብሄረተኝነት ነጻ የሆኑ ሁሉም ብሄሮች የእኔም ትግል ነው ብለው ይደግፉታል። አዲስ አበባን ጨምሮ በብዙ ህብረ ብሄራዊ ከተሞች ውስጥ የፋኖ ትግል በከተማው ህዝብ ይደገፋል።

ፋኖ የሚያነግበው የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ ስለሆነ፣ ፋኖ ታሪኬ፣ ኃይማኖቴ፣ እሴቴ፣ ትውፍቴ የሚለው የመላው የኢትዮጵያኖች ታሪክን ስለሆነ፣ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ በፋኖ ትግል ውስጥ እስከ አመራር ድረስ ለመሳተፍ በሩ ክፍት ስለሆነ (ከወላይታ ተወላጁ እንቁ ኢትዮጵያዊው ከጋሽ ታዲዎስ ታንቱ በላይ የሚወደድ የፋኖ መሪ ማግኘት ከባድ መሆኑን ልብ ይሏል)፣ ….ፋኖ ከሌሎቹ የነጻ አውጪ ድርጅቶች ይለየዋል።

እነዚህ መገለጫዎች የፋኖን ትግል ከሌሎች ብሄርተኛ ትግሎች በመለየት የህልውና ትግል ያደርጉታል።

፭. ማጠቃለያ

በአንድ ወቅት እውቁ ኢትዮጵያዊ ዶ/ር ፍቅሬ ቶሎሳ የብሄር ፓለቲካ አምረህ እየተቃወምክ፣ አብን ( አማራ ብሄራዊ ንቅናቄን) መደገፍህ እርስ በእርስህ የምትቃረን መርህ አልባ ግለሰብ አያደርግህም ወይ ብሎ ሲጠየቅ፤ መልሱ አማራው “ስጋው” አማራ አማራ ቢል “ነፍሱ” ኢትዮጵያ አትዮጵያ እንደምትል እርግጠኛ ስለሆንኩኝ ነው ብሎ መለሰ። ይሄ አባባል የአማራው ትግል የህልውና እንጂ የብሄረተኝነት ትግል እንዳልሆነ እንደ ምሳሌ ሊወሰድ ይችላል።


Opinions expressed by contributors are their own. Ethiofact does not endorse and is not responsible for the accuracy of any of the views expressed in the content on this site.

guest

0 Comments
Oldest
Newest Most Voted
Inline Feedbacks
View all comments

0
Would love your thoughts, please comment.x
()
x