Logo

“የነጭና ጥቁር” ፖለቲካችን እንክርዳድ ሲበጠር!

December 23, 2010

“ሕዝብ” ለሚለው ቃል ወይም ጽንሰ ሃሳብ ሁሉንም ፖለቲከኞች የሚያስማማ አንድ ዓይነትና ወጥ ትርጓሜ ማስቀመጥ አስቸጋሪ ነው። በእኛ ሀገር ብቻ ሳይሆን በሌሎችም ሀገሮች (ባደጉ ሀገሮች ጭምር) ያሉ ፖለቲከኞች “ሕዝቡ ጠልቷል፣ ህዝቡ መርጧል፣ ሕዝቡ እንዲህ ብሏል፣ ሕዝቡ… ህዝቡ…” እያሉ መናገር የተለመደ ነው።

ሁሉም የፖለቲካ መሪዎችና ፖለቲከኞች በዙሪያቸው ተሰባስበው ድጋፋቸውን የሚገልጹላቸውን ሰዎች “ሕዝብ” እያሉ መጥራትን ያዘወትራሉ። ይህ ዓይነቱ ድርጊት ‘የያዝኩት አቋም፣ የማራምደው ፖሊሲ፣… የብዙሃን ይሁንታ ያለው ነው’ እንደማለት የሚቆጠር፤ ራስን የማግዘፍና የማግነን የፖለቲካ “ጥበብ” ይመስለኛል። መቼም አንድ ፖለቲከኛ “የያዝኩትን አጀንዳ ብዙሃኑ አይወደውም፣ አይቀበለውም” የሚል አቋም ይዞ ትግል ሊጀምር አይችልም።

በዚህም ምክንያት፤ ደርግም፣ ኢህአዴግም፣ ቅንጅትም፣ መኢሶንም፣ ኢህአፓም፣ ኢዴፓም፣ አንድነትም ሆነ መድረክ፣… “ሕዝቡ ይደግፈኛል፣ ከጎኔ ነው፣ መርጦኛል፣…” ሲሉ እንጂ “ይጠላኛል…” ሲሉ ታይቶም ተሰምቶም አያውቅም። እኔም ይህንኑ ‘የፖለቲከኞች ቋንቋ’ በመጠቀም ሃሳቤን ገለጽኩ። እንዲህ ማድረጌ ትክክል ሊሆን ባይችል እንኳ ‘ስህተት ነው’ ለማለትም የሚቻል አይመስለኝም።

እንዲያው ለነገሩ “ሕዝብ” ማለት የስንት ሰዎች ስብስብ ነው? የአስር? የመቶ? የሺህ? የአስር ሺህ? የመቶ ሺህ? የሚሊዮን? ወይስ…? ቁርጥ ያለ ቁጥር አስቀምጦ ‘ህዝብ ማለት ይህን ያህል ነው’ ማለትስ ይቻላል? በበኩሌ የሚቻል አይመስለኝም።

ስለሆነም፣ ጌታቸው ፀሐይም ሆኑ ሌሎቻችን ሰፊ ሃሳብ ከያዘ መጣጥፍ ውስጥ አንዲት ቃል መዘን በማውጣት ‘መጀመሪያ በዚህ ጽንሰ ሃሳብ እንስማማና ከዚያ ወደ ቀጣይ ውይይት እንግባ’ ማለት፤ በልጅነታችን ‘ከእንቁላልና ከዶሮ ቀድሞ የመጣው የቱ ነው?’ እያልን እንከራከር እንደነበረው ዓይነት መግባባት የሌለው ውሃ ወቀጣ ውስጥ ገብቶ መንቦራጨቅ ስለሆነ፣ በበኩሌ እንዲህ ዓይነቱን ‘ድንቅ ፍልስፍና’ ለጊዜው ትተን በተነሳው መሰረታዊ ሃሳብ ዙሪያ ብንከራከር ይሻላል እላለሁ።

ጌታቸው ፀሐይ “አንተ ራስህ ጥቁርና ነጭ ባይ ነህ” ያሉትን በተመለከተ፣ ይህንን ለማለት ትንሽ የቸኮሉ መሰለኝ። ምክንያቱም፣ አንደኛ እኔን በአካል አያውቁኝም። ሁለተኛ በጽሑፌ ላይም ቢሆን እንዲህ ዓይነት ድምዳሜ ላይ የሚያደርስ ሃሳብ አልተንጸባረቀም። አቋም ከተባለ በጽሁፌ ላይ የሚስተዋለው፤ “ፖለቲካችን ሁለት ቀለም (ጥቁርና ነጭ) ብቻ አደለም። ቢያንስ ቢያንስ በጥቁርና ነጭ መሀል ‘ግራጫ’ ቀለም ይኖራል” የሚል መንፈስ ነው። ወደፊት ደግሞ አቋሜ ግልጽ እየሆነ መምጣቱ አይቀሬ ነው። ይህንን በዚሁ ላቁምና ወደ ዛሬው ርእሰ ጉዳይ ላምራ!

ባለፈው ጽሑፍ፣ የተቃውሞ ፖለቲካችንን ሂደት እስከ ህገ መንግስቱ መውጣትና ኢህአዴግ በተቃውሞው ጎራ የተሰለፉትን የፖለቲካ ኃይሎች ሰብስቦ አንድ ቅርጫት ውስጥ በመክተት “የደርግ ስርዓት ርዝራዦች እና የትምክህተኞች ጎራ” ብሎ መፈረጁንና እንዲህ ዓይነት የፖለቲካ መካረርና ጡዘት በተፈጠረበት ወቅት በአዲስ ትውልድ የተገነባው፣ አዲስ አስተሳሰብ ያነገበውና አዳዲስ አሰራሮችን የሰነቀው «ኢዴፓ» ብቅ ማለቱን ገልጨ ነበር በቀጠሮ የተለየሁት።

የዚህ ጸሑፍ አቅራቢ እስከ 1991 ዓ.ም ድረስ ምንም ዓይነት የፖለቲካ ተሳትፎ ሳይኖረው የሀገሪቱ ፖለቲከኞች የሚያደርጉትን መራኮት ከርቀት ሲከታተልና ሲታዘብ ቆይቷል። በዚህ ሁኔታ ላይ እንዳለሁ ኢዴፓን ከመሰረቱት ወጣቶች አንዱ ጋር በአንድ ጓደኛየ አማካይነት ከሶስት ዓመታት በፊት ዩኒቨርሲቲ ውስጥ እንተዋወቅ ስለነበር፣ በ1991 ዓ.ም ስልክ ደወለልኝና ለአንድ ጉዳይ እንደሚፈልገኝ ገለጸልኝ። ካዛንቺስ ቶታል አጠገብ ባለች አንዲት ቡና ቤት ለመገናኘት ተቀጣጠርን።

በቀጠሯችን መሰረት በተገናኘንበት ወቅት በሀገራችን ወቅታዊ ሁኔታ ዙሪያ ማውራት ጀመርን። በስልጣን ላይ ያለው መንግስት እያደረሰ ያለውን ጥፋት ዘረዘርን። ትክክል ባለመስራቱም አወገዝነው። ይኸው ወጣት ቀጠለና ‘እነዚህን ችግሮች መዘርዘርና ኢህአዴግን ዝም ብሎ ማውገዝ ትርጉም የለውም’ አለና እሱና ጥቂት ወጣቶች እየተሰባሰቡ መሆኑን በመግለጽ እኔም ይህንን ስብስብ ተቀላቅዬ እንድታገል ጠየቀኝ።

በዚህ መልኩ ወደ ሀገሬ ፖለቲካ ዘው ብየ ገባሁ። ባላሰብኩትና ባልጠበቅኩት ሁኔታ የሀገሬ ፖለቲካ የግንባር መስመር (Front Line Politics) ተሰላፊ ሆንኩ። እናም፣ በዚህ ጽሁፍና በቀጣይ ጊዜአት በማቀርባቸው መጣጥፎች ውስጥ የማሰፍረው ሃሳብ “በስማ በለው” ያገኘሁት ሃሳብ ሳይሆን፤ በዓይኔ አይቼ፣ በጆሮዬ ሰምቼ ያረጋገጥኩትና የተሳተፍኩበት ነው። በዚህም ምክንያት ስጽፍ ስሜቴ እውነትን እንዳይጋፋ አስፈላጊውን ጥንቃቄ ሁሉ አደርጋለሁ።

የሀገራችንን ሁለት ጽንፍ ላይ የተንጠለጠለ “የነጭ” እና “የጥቁር” ፖለቲካ ምዕራፍ በመዝጋት የሶስተኛ አማራጭ መኖርን ብስራት ያስተጋባው ኢዴፓ ነው። ኢዴፓ ይህንን የሶስተኛ አማራጭነት መርህና አስተሳሰብ ለምንና እንዴት ሊያቀነቅን ቻለ? ለሚለው ጥያቄ ምላሽ ለማግኘት ይቻል ዘንድ በኢዴፓ የምስረታ ሂደት የነበሩትን ሁኔታዎች በአጭሩ መመልከት ጠቃሚ ነው የሚል እምነት አለኝ።

ኢዴፓ ህጋዊ ሰውነት አግኝቶ ከመቋቋሙ በፊት በምስረታው ሂደት የተሳተፉ ወጣቶች ረጅም ጊዜ የወሰደና በርካታ ጉዳዮችን የዳሰሰ ውይይትና ምክክር አድርገዋል። በዚህ ወቅት ከተነሱት መሰረታዊ ጥያቄዎች ውስጥ “በሀገራችን የተቃውሞ ፖለቲካ ውስጥ ለመሳተፍ ምን አማራጭ አለን?” የሚለው ቀዳሚ ነበር።

ለዚህ ጥያቄ በወቅቱ የሰጠነው መልስ “ሁለት አማራጭ አለን። አንዱ አማራጭ፣ በጊዜው ከነበሩት ፓርቲዎች ውስጥ የአንዱ አባል በመሆን ኢህአዴግን መታገል (ውጫዊ ትግል ማድረግ) እንዲሁም አባል በምንሆንበት ፓርቲ ውስጥ ውስጣዊ ትግል ማድረግ የሚል ሲሆን፤ ሁለተኛው አማራጭ ደግሞ ለዘመኑ ፖለቲካ የሚመጥን በአዲስ አስተሳሰብ የተቃኘ አዲስ ፓርቲ በማቋቋም ኢህአዴግንም፣ ሌሎች ተቃዋሚ ፓርቲዎችንም፣ የኢህአዴግ አጋሮችንም መታገል የሚል ነበር።

ከብዙ ክርክር በኋላ ሁለተኛው አመራጭ ተቀባይነት በማግኘቱ ለአዲስ ፓርቲ ምስረታ የሚሆን ዝግጅትና የውይይት መድረክ ተከፈተ። ይህም የምክክርና የውይይት መድረክ በየሳምንቱ እሑድ እሑድ ለአርባ ስምንት ሳምታት ተካሄደ። (በዚህ ውይይት ወቅት የተነሱ ነጥቦችና ስምምነት ላይ የተደረሰባቸው ጭብጦች በቃለ ጉባዔ እየሰፈሩ የፓርቲው ፕሮግራምና ደንብ ሲረቀቅ የመነሻ ሃሳብ እንዲሆኑ መደረጉን ልብ ይሏል)

በዚህ የውይይት ሂደት በቀዳሚነት ተነስቶ ውይይት የተደረገበት ጥያቄ፤ ‘እስከ አሁን ድረስ የተመሰረቱ ፓርቲዎች (ገዢው ፓርቲ ጭምር) ድክመትና ጥንካሬ ምንድን ነው?’ የሚል ሲሆን፤ በዚህም ጊዜ፡-

•    የየፓርቲዎቹ ፕሮግራም፣ ደንብና የሚከተሉት ርእዮተ ዓለም፣ ጠንካራና ደካማ ጎን፣
•    የየፓርቲዎቹ አባላት አመለካከትና የትግል መንፈስ ጠንካራና ደካማ ጎን፣
•    የየፓርቲዎቹ አመራር አባላት አመለካከትና ባህሪ ጠንካራና ደካማ ጎን፣
•    የየፓርቲዎቹ አደረጃጀት፣ መርሆዎችና አሰራር ጠንካራና ደካማ ጎን፣

ወዘተ. የመሳሰሉትን ጉዳዮች በዝርዝር በመቃኘት፣ ሲወርድ ሲዋረድ የመጣውን “የጥቁር” እና “የነጭ” ፖለቲካችንን በማበራየት ምርቱን ከግርዱ፣ ፍሬውን ከእንክርዳዱ የመለየት ጥረት ተጀመረ። (ክፍል 4 ይቀጥላል)

Share

3 comments on ““የነጭና ጥቁር” ፖለቲካችን እንክርዳድ ሲበጠር!

  1. WE need development, we don’t carea bout different system and oppinions the so called balh blah…
    1. Monarchay-fail
    2. Millitary-fail
    3.Democracy- can not commet at this time, we will see what happens, most Ethiopians need BREAD not diasporas poltics and pal-talk jazz music. Bye-Bye

  2. Who said democracy is the only solution for the people? most of the world is not believe in democracy such as China ,middle east,Russia …so what?Democracy is all about wealthy ,power,and prestige other thnking is illusion.

  3. አቶ መርጉ በዚህ ጽሑፍ እያስረዱን የሚገኙት ትንታኔ የሚመች ነው::ኢዴፓ ከሌሎች ፓርቲዎች ለየት የሚልባቸው ብዙ ገጽታዎች አሉት:: እነዚህን የፓርቲውን መለያዎች በሚገባ ያላጤኑ ሰዎች የፓርቲውን የትግል ሂደቶች በትክክል ለመረዳት ባለመቻላቸው ድርጅቱን በአጉል ሲፈርጁ ይታያሉ:: ነገር ግን አንድ ድርጅት የሚያደርጋቸው እንቅስቃሴዎች ከማንነቱ የሚመነጩ በመሆናቸው (የድርጅቱን ማንነት: የቆመላቸውን ዓላማዎች; ፍልስፍናውን; ፕሮግራሙን መርሖቹንና ፖሊሲዎቹን )ካልተረዳን በስተቀር ትክክለኛ የሆነ አስተያየት ወይም ፍርድ ለመስጠት አዳጋች ነው:: በተለይም ኢዴፓ እስካሁን ድረስ ባገራችን ከተለመደው የፖለቲካ መለኪያ ለየት ያለ ይዘትና አቀራረብ ይዞ የመጣ ፓርቲ ስለሆነ ለማድነቅም ሆነ ለማውገዝ ድርጅቱ የረገጠበትን መሰረት በሚገባ መረዳት የግድ ይላል:: ስለሆነም አቶ መርጉ ውሃን ከጥሩ ነገርን ከሥሩ በማቅረባቸው ለመረዳት ለሚፈልግ መልካም መንገድ አመልካች ነው::

Comments are closed