General Yohanes

“አዙሪት፣” የመጽሃፍ ግምገማ

የመጽሃፍ ግምገማ፤ ክፍል 1

የመጽሃፉ ርዕስ፤ አዙሪት

ደራሲ፤ ሌ/ጄኔራል ዮሃንስ ገ/መስቀል

በአበራ ገ/ማርያም

የሌ/ጄኔራል ዮሃንስ ገ/መስቀልን አዙሪት የሚለውን መጽሃፍ አንብቤ ስጨርስ፣ በመጽሃፉ ውስጥ በተነሱ ከዚህ በታች በተዘረዘሩ ነጥቦች ዙርያ ግምገማ ብሰጥ ሕወሃትን፣ ሕወሃት ያደራጀውን ጦርን፣ የሕወሃትና የሻዕቢያን የጌታና የሎሌ ግኑኝነት፣….ይበልጥ ለመረዳት ይጠቅማል ብዬ ገመትኩኝ።

1. የሕወሃት “ባህላዊ ጄኔራሎች”

ሕወሃት ከፕሪቶሪያ ስምምነት በኋላ የደብረጽዮንና የጌታቸው ረዳ ቡድን ተብሎ ለሁለት ሲሰነጠቅ፣ በጌታቸው ረዳ ደጋፊዎች አብዛኛው የሕወሃት ጄኔራሎች ከደብረጽዮን ጋር ስለቆሙ “ባህላዊ ጄኔራሎች” እያሉ ማንቋሸሽ ተጀምሮ እዚህ ተደረሰ።

መለስ ዜናዊ በህይወት እያለ፣ ጦሩ በህገ መንግስቱ መሰረት መንቀሳቀሱን የሚቆጣጠር የመከላከያ ካውንስል ተቋቁሞ ነበር። ለምን ታዋቂ የጦር ት/ቤት ገብተው የጦር ትምህርት አይሰለጥኑም ብሎ የሚሊቴሪ ካውንስሉ መለስን ሲጠይቅ፣ እኛ የአጼ ኃ/ስላሴን ስህተት አንደግምም። አጼ ኃ/ስላሴ የተገለበጡት በከፍተኛ ደረጃ ውጪ ድረስ ልከው ባስተማሯቸው መኮንኖች ነው። ስለዚህ ውጪ ልከን አናስተምራችሁም አለ (ገጽ 254 – 255)። በእንዲህ አይነት ውሳኔ ነበር መለስ ዜናዊ ታማኝ ከዘመናዊ የሚሊቴሪ እውቀት የተፋቱ “የባህላዊ ጄኔራሎች” መሰረት የጣለው። “ባህላዊ ጄኔራሎች” ባጭሩ የመለስ ትሩፋቶች ናቸው።

ካውንስሉ የሚያነሳቸው እንዲህ ዓይነት ጥያቄዎች ያሳሰበው መለስ ዜናዊ፣ የሚሊቴሪ ካውንስሉን ደረጃ ዝቅ አድርጎ ለኢታማዦሩ አማካሪነት ብቻ እንዲያገለግል ወሰነ። ምክሩን አስፈላጊ መስሎ ሲታየው ብቻ የወቅቱ ኢታማዦር ሹም ሳሞራ ዩኑስ እንዲቀበል አዘዘ። ብዙም ሳይቆይ፣ እቺ ባቄላ ካደረች አትቆረጠምም ብሎ፣ መለስ ዜናዊ “መተካካት” የሚል የማይፈልጋቸውን የጦሩ መሪዎችን ማባረሪያና ማሸማቀቂያ አሰራር ቀየሰ።

እኔ ከዚህ የመለስ ንግግር ጋር ነው “ባህላዊ ጄኔራል” ትርጉም የሚሰጠኝ። መለስ “የባህላዊ ጄኔራሎች” ፈጣሪ መሃንዲስ መሆኑን ልብ ማለት ያስፈልጋል። ካለምንም የሚሊቴሪ ሳይንስ ትምህርት የኢትዮጵያን ፕሮፌሽናል ጦር አፍርሰው “በባህላዊ ጄኔራሎች” ሙሉ ለሙሉ ተኩት።

በተለይ የአጼ ኃ/ስላሴ፣ እንዲሁም የተወሰኑ የደርግ ጄኔራሎች አንቱ በተባሉ እንደ ሳንድኽርስትና ዌስት ፖይንት ስመ ጥር የጦር አካዳሚዎች የተማሩ ነበሩ። የአፄ ኃ/ስላሴ የሀረር ጦር አካዳሚ እራሱ ዘመናዊ የጦር አመራር ማፍለቂያ ተቋም ነበር።

ለሕወሃት የጦር አመራሮች ግን ለመጀመርያ ጊዜ ከጎሪላ ውጊያ ውጪ conventional ጦርነት ምን እንደሚመስል ያስተማሯቸው፣ ደርግ ሊወድቅ አካባቢ የተማረኩት ኮ/ል ሠረቀ ብርሃንና ጄኔራል በርታ ገሞራው መሆናቸው እራሳቸው ይመሰክራሉ። የባድመ ጦርነት በድንገት ሲከሰት፣ አዋርደው በትነው ለማኝ ያደረጉትን የኢትዮጵያን የቀድሞ ጦር ነበር ፤ እግር ላይ ወድቀው ለምነው የማያውቁትን conventional ውጊያ ከሻዕቢያ ጋር ተዋግቶላቸው በስልጣን የሰነበቱት።

የቡሬና የጾረና ግንባር እልቂቶች “የባህላዊ ጄኔራሎች” ማሳያ ተደርገው ሊወሰዱ ይችላሉ።

ከባድመ ድል በፊት፣ በወቅቱ የኢታማዦር ሹም የነበረው ጄኔራል ጻድቃን፣ በጾረና ግንባር ከሻዕቢያ ጋር ውጊያ ገጥሞ ከፍተኛ እልቂት አስከትሎ ኢትዮጵያን ለከፍተኛ ሽንፈት ዳረገ። የሽንፈቱ ደረጃ በጣም ትልቅ ስለነበር፣ ፃድቃን ከኃላፊነት ተነስቶ ጄኔራል ሳሞራ ዩኑስ የኢታማዦር ሹም በሕወሃት ተደረገ (ገጽ 94 – 95)።

ጄኔራል ታደሰ ወረደም እንዲሁ በቡሬ ግምባር በእነ ስዬ አብርሃ ትዕዛዝ አሰብን እንዲይዝ በሚስጥር ትዕዝዝ ተሰጥቶት፣ የኢትዮጵያን ጦር ቄራ እንደ ገባ በሬ አስጨረሰ (ገጽ 122 – 123)።

በሁለቱ “ባህላዊ ጄኔራሎች” ጻድቃንና ታደሰ ወረደ የተመራው የጾረናና የቡሬ ውጊያ በከፍተኛ ሽንፈት ከተደመደመ በኋላ ነበር፣ እንደ አዲስ በባድመ ግምባር አዲስ ማጥቃት ተከፍቶ በስተመጨረሻ የሻዕቢያ ጦር ብትንትኑ ወጣ።

2. የሻዕቢያ ለሕወሃት ስር የሰደደ ንቀት ምንጩ ምን ይሆን?

በሕወሃት ውስጥ አዋቂዎች አንድ ተደጋግማ የምትጠቀስ አባባል አለች። መለስ ሲያድግ ማንን መሆን እንደሚፈልግ ሲጠየቅ ኢሳያስን፣ ሕወሃት ደግሞ እንደ ድርጅት ሻዕቢያን መሆን እንደሚፈልግ ይነገራል። በአንድ ወቅት መለስ ከዚህም በላይ አልፎ ሄዶ፣ ዩኑቨርስቲ ገብቶ ከመማር ይልቅ፣ የኢሳያስን የቀናቶች ዲስኩር መስማት ብዙ ያስተምራል እያለ በኩራት ይናገር ነበር ይባላል።

በአንድ ወቅት የሕወኃት ምክትል መሪ የነበረው ግደይ ዘርዓጽዮን ……..በሚለው መጽሃፉ፣ ልምድ ለመቅሰም ስንል ሻዕቢያን ከኤርትራ ባድመ ድረስ እየጋበዝን ከሻዕቢያ ጎን እየተዋጋን፣ የሚማረኩ ከባባድ መሳሪያዎች በሙሉ ሕወሃት ልምድ ከቀሰመ ይበቃዋል ብሎ፣ ሻዕቢያ እንደሚወስደው ጽፏል።

ጸሃፊው የቀይ ኮኮብ ዘመቻን ለማክሸፍ፣ 2 ብርጌድ የያዘ የሕወሃት ጦር ሻዕቢያን ለመርዳት ወደ ኤርትራ ሳህል እንደተላከ ይገልጻል። አንዱ 43ኛ ብርጌድ በውስጡ ፀሃፊውን፣ ሳዕረ መኮንንን፣….ሌላኛው ብርጌድ ደግሞ እነ ሳሞራ የኑስን የያዘ ነበር። ሳህል ሲደርሱ፣ ሻዕቢያ እራሳችሁን ችላችሁ መዋጋት እውቀቱም ብቃቱም የላችሁም ብሎ፤ ሳዕረ መኮንን፣ ግንዲ ሑቆን፣ ፀሃፊውን ጠዊል በሚባል የሻዕቢያ አዛዥ በታች ስር ሆነው እንዲዋጉ ተደረገ። እነ ሳሞራ የኑስ ደግሞ እንዲሁ በሌላ የሻዕቢያ አዛዥ ስር ሆነው አመራር እየተቀበሉ የሻዕቢያን ጦርነት በኤርትራ እንዲዋጉ ተደረገ። ይሄን ንቀት በቀይ ኮከብ ዘመቻ ወቅት የሳህል የሕወሃት የበላይ አስተባባሪ ተደርጎ የተላከው ስብሃት ነጋና የሕወሃት የማዕከላዊ ኮሚቴ ጉዳይ አስፈጻሚው አርከበ እቁባይ በሚገባ ያውቁታል (ገጽ 24 -25)።

ነገርን ነገር ያነሳዋል እንዲሉ፣ በኮሪያ ዘመቻ ጊዜ ጄኔራል አማን አንዶም ምዕራባውያን የኢትዮጵያን ጦር ንቀው፣ በሌላ አገር ጦር አዝማች ስር ሆናችሁ ተዋጉ ሲባሉ፤ እኛ እራሳችንን ችለን የራሳችን ግዳጅ ተሰጥቶን የምንዋጋ ነጻ ጀግና ህዝብ ነን ብለው ፣ በስተመጨረሻ አንድ ወታደር ሳይማረክባት ኢትዮጵያኖች ትልቅ ታሪክ በኮርያ ዘመቻ ሰሩ።

ሕወሃት ውስጥ ሻዕቢያን ቀና ብሎ የሚያይ ጄኔራል አማንን የመሰለ በራሱ የሚተማመን አንድ የጦር አዛዥ ነው የጠፋው። ሁለቱ የኢትዮጵያ ጦር ኢታማዦር ሹም የነበሩት ሳዕረና ሳሞራ ሳይቀሩ፣ ሻዕቢያ አቅም የላችሁም ብሎ በሻዕቢያ አዋጊዎች ስር ሆነው የተዋጉ መሆናቸው፣ በቀድሞው የሕወሃት ምክትል መሪ ግደይ ዘርዓጽዮን ምስክርነት፣ የሕወሃት ተዋጊዎች ልምድ ለመቅሰም በሚል ከሻዕቢያ ጎን ተሰልፎ መዋጋትን እንደ ክብር መቁጠራቸው፣…. የሻዕቢያ ለሕወሃት ተዋጊዎች ንቀት መሰረቱ ሊሆን ይችላል።

3. እውን ፀሃፊው ማንም የሚጋልበው አድርባይ ነው?

ጸሃፊው በመጀመርያው የብልጽግና ሹመት የትግራይ ጊዝያዊ አስተዳደር የወታደራዊ ጉዳዮች ኃላፊ ሆኖ በአብይ በመሾሙ፣ በተለይ የሕወሃት ደጋፊዎች ከሃዲ፣ አድርባይ፣ አቋም የለሽና ሆድ- አደር አድርገው ይስሉታል።

ነገር ግን በዚህ ክስ ላይ መሬት ላይ ያለው ሃቅ የተወሰኑ ናሙና ምሳሌዎች በመስጠት ምን እንደሚመስል ለማሳየት እሞክራለሁ። በመጀመሪያ ሻዕቢያ በሳህል በረሃ በቀይ ኮኮብ ዘመቻ ወቅት በስሩ የነበሩትን የሕወሃት ተዋጊዎችን ሲያጎሳቁልና (የፊጥኝ አስሮ ግርፊያን ይጨምራል) አድልዎ ሲያደርግ (እረፍት ለሻዕቢያ ተዋጊዎች ሰጥቶ ለሕወሃት ተዋጊዎች መከልከል) ፀሃፊው አይቶ፣ ባልተለመደ ሁኔታ ቅሬታውን በግልጽ በመግለጹ፤ ከሳህል ወደ ትግራይ የተባረረ ብቸኛ የሕወሃት አዋጊ ነበር። ለምን የሻዕቢያ የንቀት አሰራር ላይ ተቃውሞ አነሳህ ተብሎ ለመለስ፣ ለአርከበና ለስብሃት ነጋ ፀሃፊው ቃል ሰጥቷል፣ ተገስጿል። ማስፈራርራትም ደርሶበታል (ገጽ 31- 44)።

ሁለተኛ አብይና ኢሳያስ በፍቅር ብን ባሉበት ወቅት፣ የኢትዮጵያ መንግስት የኤርትራ ጦር ኢትዮጵያ ውስጥ አልገባም እያለ በሚያስተባብልበት ጊዜ፤ የአብይ ሹመኛ ሆኖ እየሰራ ከአብይ ፍላጎት በተጻራሪ የኤርትራ ጦር ኢትዮጵያ ውስጥ ገብቷል ብሎ እውነቱን በመናገር ፀሃፊው የመጀመርያው ሰው ነው (ገጽ 371)።

ሶስተኛ በአብይ የስልጣን የመጀመርያ ወራቶች የኦሮሞ የፀጥታ ኃላፊ ሆኖ የተሾመው ጄኔራል ከማል ገልቹ፣ ከትግራይ ወደ ኤርትራ ጦር ይዞ ከመጥፋቱ በፊት፣ እንደ ላይቤርያ የሰላም አስከባሪነታቸው የሚገባቸውን 25% ክፍያ ባለማግኘታቸው የተነሳውን ውዝግብ ተከትሎ፣ በፍቼ ሊያነጋግራቸው የመጣውን የሕወሃት የጦር አለቃ አግቶ በማቆየቱ፣ ጄኔራል ሳሞራ ዩኑስ ለፀሃፊው ደውሎ ጄኔራል ከማል ገልቹን እንዲያስረው ትዕዛዝ ሰጥቶ ነበር። ፀሃፊው በምን ህግ? የት የህግ ማቆያ ቦታ ለማስቀመጥ? ብሎ ጠይቆ አላስርም አለ። ብዙም ሳይቆይ ጄኔራል ከማል ገልቹ የተወሰኑ የኦሮሞ ወታደሮችን ይዞ ወደ ኤርትራ በመጥፋቱ፣ ፀሃፊው የሕወሃት ባለስልጣኖች ጠርተው እንዳነጋገሩትና፣ ትግሬ መሆኑ አተረፈው እንጂ ኦሮሞ ቢሆን ኖሮ ትልቅ ችግር ውስጥ ሊወድቅ ይችል እንደነበር ያትታል (ገጽ 32 እና 262).

አራተኛ የባድመ ጦርነት በ1990 ሊጀመር አካባቢ ፀኃፊው ለጄኔራል ጻድቃን ደውሎ ሻዕቢያ በእርግጥ ሊወረን እየተዘጋጀ ነው ሲለው፣ ጄኔራል ፃድቃን ከኤርትራ መከላከያ ሚንስትር ጄኔራል ኤፍሬም ጋር እየተነጋገርን ስለሆነ “አታጋን” ብሎ ለፀሃፊው መልስ ሰጠ። ቀጥሎ ፀሃፊው
ከኢዲግራት የባድመ ሚሊሻዎችን የሚረዱ የተወሰኑ ወታደሮች የሻዕቢያን ወረራ ለመመከት ወደ ባድመ ማንንም ሳያስፈቅድ እንዳመጣ ጄኔራል ጻድቃን ሲሰማ፣ የማንም ፍቃድ ስላላገኘህበት ችግር ውስጥ ሳትገባ በቶሎ ጦሩን መልስ ብሎ አስመልሶታል (ገጽ 86 እና 87).

እነዚህ አራት የተመረጡ ምሳሌዎች፣ ፀሃፊው የማያምንበት ከሆነ ከላይ የመጣ ትዕዛዝም ቢሆንም አሻፈረኝ ከማለት እንደማይመለስ ነው።

4. ኢትዮጵያ፣ ኢትዮጵያዊነትና ፀሃፊው

መለስ ዜናዊን ጨምሮ ቱባ ቱባ የሆኑት የሕወሃት ባለስልጣኖች ዋና የሚገለጡቡት ባህሪ የኢትዮጵያን ሰም ለመጥራት መጠየፋቸው ፣ ስለ ሀገር የግድ ማውራት ካለባቸው ደግሞ ኢትዮጵያ በማለት ፋንታ ሀገራችን ማለታቸው ነው። ፀሃፊው ግን በዚህ መጽሃፍ ላይ የኢትዮጵያን ስም ለመጥራትም ሆነ ኢትዮጵያዊ ነኝ ለማለትም ሲከብደው አይታይም።

ይቀጥላል።

guest

0 Comments
Oldest
Newest Most Voted
Inline Feedbacks
View all comments

0
Would love your thoughts, please comment.x
()
x