የአዲስ አበባ ቆይታዬና ትዝብቴ

የአዲስ አበባ ቆይታዬና ትዝብቴ (ክፍል-1)

በፍሬው አበበ

በአዲስ አበባ ወደ 2 ወር ቆይታ በኋላ ሰሞኑን ወደ ስደት ተመልሻለሁ። በቆይታዬ ጊዜ የታዘብኩትን ላካፍላችሁ።

1. “ሸገር”

በአዲስ አበባ ስም ኦህዴዷ አዳነች አቤቤና የኦህዴዱ ሽመልስ አብዲሳ ተስማሞተው፣ የአዲስ አበባን ህዝብ የበይ ተመልካች በማድረግ አዲስ አበባ ዙርያውን በአፓርታይድ ባንቱስታን አጥረው ባልጠፋ ስም “ሸገር” ብለዉታል። የእነዚህ የሁለት ኦህዴዶች ስምምነት ውጤት የሆነው “ሸገር” የስም አሰያየሙ ሳይቀር ተንኮል እንዳለበት ግልጽ ነው።

ሀ. “ለሸገር” ነዋሪዎች ብሄር ኦሮሞ የሚል መታወቂያ መሰጠት።

አዲስ አበባና ዙርያዋ አማርኛ ተናጋሪ የሚበዛባቸው ከተሞች ናቸው። ጆሞ ቁጥር 1 እና 2 በአብዛኛው ከ4 ኪሎ የተነሱ አዲስ አበቤዎች የሚኖሩበት ቦታ ናቸው። መለስ ዜናዊ እንደ ሸዋ ህዝብ አብዝቶ የሚጠላው አልነበረምና፣ የ4 ኪሎ ህዝብ ደግሞ በአብዛኛው ከሸዋ ሚኒሊክን ተከትሎ አዲስ አበባ ስትቆረቆር የከተመ ስለነበረ፣ መጀመርያ ያፈናቀለው የ4 ኪሎን ህዝብ ወደ ጀሞ ነበር። በሕወሃት ታሪክ ውስጥ ከመሃከላቸው ለኢትዮጵያ የሚቆረቀር ሰው ሲገኝ፣ “ሸዌ” እየተባለ በእነ መለስ ይጣጣል፣ ይሽሟጠጥ ነበር።

የመለስ ሊጋሲ አስቀጣዩ ኢህአዴግ ቁጥር 2 ኦህዴድ ደግሞ፣ ጆሞ ቁጥር 2ን ሺመልስ አብዲሳ በጉልበቱ ወደ ኦሮሞ የአፓርታይድ ባንቱስታን ጨምሮታል። ቦታው ላይ ሙሉ ለሙሉ በሚባል መልኩ የሚኖረው ህዝብ አማርኛ ተናጋሪ ነው። ነዋሪው ኦሮምኛ አይሰማም። ነገር ግን ቋንቋው፣ አገልግሎቱ ፣ ….የሚሰጠው በኦሮምኛና በቁቤ ነው።

በጣም የገረመኝ አብሮ አደጌ የሰፈሬ ልጅ በእናቱም በአባቱም ኤርትራዊ የሆነና ጆሞ ቁጥር 2 የሚኖር፣ መታወቂያዬ ላይ ብሄር የሚለው ኦሮሞ ነው አለኝ። እንዴት፣ ለምን ብዬ ጠየኩት። ካላመንክ መታወቂያዬን እይ ብሎ ሰጠኝ። መታወቂያውን አየሁት። የተጻፈው በቁቤ ነው። ምን እንደሚል እንኳን አያውቅም። መታወቂያውን ስንቀበል ምን እንደሚል ስለማይገባን፣ ስማችንና የልደት ቀናችን ትክክል መሆኑን ብቻ ነው የምናረጋግጠው አለኝ።

ከ4 ኪሎ ወደ ጆሞ 2 የከተምነው ከተለያየ ብሄረሰብ የተወልድነው (ከአማራ፣ ከኤርትራ፣ከትግራይ፣ ከሱማሌ፣ ከአደሬ፣ ከደቡብ፣ ….) የአዲስ አበባ ልጆች በሙሉ ብሄራችንን ሳይጠይቁን ኦሮሞ ብለው መታወቂያችን ላይ ሞልተውታል አለኝ። እኔ ኤርትራዊው ብሄሬ ኦሮሞ ተብሎ ሲሞላ ምን ማለት ይቻላል አለ። ለምን ብለን ብንጠይቅ አርፋችሁ ተቀመጡ ተባልን። የሽመልስ አብዲሳ ኦህዴድ ይሄን ያህል አይን ያወጣ ቅንጣት ያህል ይሉኝታ የሌለው የወሮበላ ጥርቅም ነው አለኝ።

ይሄ ኤርትራዊ ጓደኛዬ በቅርቡ ፋይዳ መታወቂያ ስለማወጣ ቢያንስ ብሄሬ ኦሮሞ ተብሎ ፋይዳ መታወቂያ ላይ ስለማይጻፍ ግልግል ነው አለ።

ለምን ይመስልሃል ኦሮሞ ሳትሆን መታወቂያህ ላይ ኦሮሞ ብለው የጻፉት ስለው፣ ወደፊት የአካባቢው ህዝብ በሙሉ ኦሮሞ ነው ብለው ይሄን እንደ ማስረጃ በማቅረብ ድብቅ የፓለቲካ ፍላጎታቸውን ሊያሳኩ ነው አለ።

ይሄ እንዲህ ዓይነት አይን ያወጣ ማጭበርበር ግን የትም አያደርስም። መንግስት መቀየሩ አይቀርም። ያኔ እነዚህ ዜጎች እማኝ ምስክሮች ይሆናሉ። የህዝብ ቆጠራ ኦህዴድ በስልጣን እያለ ከተካሄደ፣ ትክክለኛ ብሄራቸውን ቆጠራው ላይ እንዴት እንደሚያስሞሉ ከአሁኑ በቅጡ መታሰብ አለበት።

አንድ ወቅት፣ ነፍሳቸውን ይማረውና፣ ዶ/ር በየነ ጴጥሮስ አርሲ ተብሎ ወደ ኦሮሞ የአፓርታይድ ባንቱስታን ክልል ውስጥ ብዙ የሃዲያ ዘመዶቻቸው እንደሚኖሩና፣ ብሄራቸው ሃድያ ሆኖ ኦሮሞ ተብለው እንደተወሰዱ ተናግረዋል። ዶ/ር ላጲሶም ተመሳሳይ ነገር ሲናገሩ ሰምቼያለሁ።

የሕወኃት ህግ ኢትዮጵያን በተለያዩ የጎሳ አፓርታይድ ባንቱስታኖች የከፋፈለው በሚናገሩት ቋንቋ እንጂ፣ በጎሳቸው አይደለም።

ስለዚህ ባለ ጊዜው ኦህዴድ “ሸገር” ብሎ ወደ ኦሮሞ አፓርታይድ ባንቱስታን ያካተታቸው ቦታዎች በሙሉ አማርኛ ተናጋሪዎች ናቸው። በሕወሃት ህግ መሰረት በፍጹም ወደ ኦሮሞ ባንቱስታን መካተት አልነበረባቸውም።

የወልቃይት ህዝብ ከአማርኛ በተጨማሪ አረብኛና ትግርኛ ስለሚናገር፣ ከአህዳዊው ሕወሃት በቅርቡ ነጻ እስኪ ወጡ ድረስ በግዳጅ የትግራይ አካል አድርጓቸው ታይቶ የማይታወቅ አፈና፣ ድብደባ፣ግድያ፣… ሲፈጽምባቸው ነበር።

የአነ በረከት ስምዖን ብአዴንም፣ በወሎ ከሚሴ ወደ 10% ያህሉ ኦሮምኛ ስለሚናገሩ ብቻ፣ የኦሮሞ ልዩ ዞን አድርገውታል። በኦሮሞ የአፓርታይድ ባንቱስታን የሚኖሩ ወደ 10 ሚሊዮን የሚጠጉ አማርኛ ተናጋሪዎች ግን አንዳችም ልዩ ዞን፣ ውክልና፣… የላቸውም።

በምን መስፈርት 10% ህዝብ ፍላጎት ከተቀረው 90% ህዝብ ባላይ ሊወሰድ እንደሚችል ብአዴን ብቻ ነው የሚያውቀው። ዲሞክራሲ ማለት የአብላጫው ህዝብ አመራር የአናሳ መብቶችን ባከበረ መልኩ የሚመሰረት ስርዓት እንጂ፣ የአናሳዎች ፍላጎት በአብላጫ ህዝብ ላይ የሚጫንበት ስርዓት አይደለም።

100% አማርኛ ተናጋሪ የሆነው የ”ሸገር” ህዝብ በየትኛው ህግ ይሆን የኦሮሞ አፓርታይድ ባንቱስታን ውስጥ የተካተተው? ካለ ጥርጥር ተረኝነት ነው።

የአለሚቱን ጠባሳ ያየ በእሳት አይጫወትም እንደሚባለው፣ የወያኔን በወልቃይት መዘዝ መንኮታኮት ያየ፣ ከዚህ ተመሳሳይ ስህተት ኦህዴድ ሊቆጠብ በተገባ ነበር። ሕወኃት ተስገብግቦ ሁሉንም ካለይሉኝታ አግበሰበሰ። ከስልጣን ቀልቡ ተገፎ ሲወገድ ሁሉንም አጣ። የተረኞቹ ኦህዴዶቹም እጣ ፈንታ ከሕወኃት አይለይም።

guest

0 Comments
Oldest
Newest Most Voted
Inline Feedbacks
View all comments

0
Would love your thoughts, please comment.x
()
x