ወልቃይት፤ የአብይና የወያኔ እስትንፋስ ማስቀጠያ
በአበራ ገ/ማርያም
፩. አብይ ለምን የወልቃይትን ጦርነት ይፈልገዋል?
የእነ ጄኔራል አሳምነው፣ ዶ/ር አምባቸው፣ ኢንጅነር ስመኝ፣… አሟሟት አሁን ድረስ እንቆቅልሽ ነው። እኔ ሳላውቅ የአብይ ኦሮሙማ ከአማራ ክልል አንድም ሰው አስሮ ይዞ ሊወጣ አይችልም አሳምነው ካለ በኋላ፣ አብይ ጥርስ ውስጥ ገባ። ጌታቸው ረዳ አሳምነውን በህይወት ይዛችሁ እንዳታቆዩት ብሎ ትዕዛዝ እንደሰጠ ተናግሯል ።
አብይ ከፕሪቶርያ ስምምነት በቀጥታ የሚመለከተውን አማራውን አገለለ። የወልቃይትና የራያ ጉዳይ አወዛጋቢ ቦታዎች ተብለው በስምምነቱ እንዲገቡ ታኮ ያስገቡት ከአማራው ለታዛቢነት የሄዱት እነ ዶ/ር ጌታቸው ስለነበሩ፤ በናይሮቢ ስምምነት አንድም አማራ እንዳይገኝ አብይ አድርጎ፣ ሕወሃት በፕሪቶሪያ ስምምነት ሙሉ ለሙሉ ትጥቅ መፍታቱ ቀረና፣ ጭራሽ ትግራይ ያለበትን የደህንነት ችግር ግንዛቤ ውስጥ በከተተ መልኩ ህወሃት ትጥቁን አያወርድም ብለው ተስማሙ ።
በአንድ በኩል ወያኔን የፕሪቶሪያን ስምምነትን በሚጻረር መልኩ ትጥቁን አይፈታም እያለ፣ በሌላ በኩል አብይ ለስልጣኔ ትልቅ አደጋ ነው ብሎ ያሰጋውን የአማራ ልዩ ኃይልን በፍጥነት በማፍረስ ለፋኖ መወለድ ዋና ምክንያት ሆነ።
የአማራ ልዩ ኃይልን ካፈረሱ በኋላ፣ ወያኔ ወደ ራያ አላማጣ እንዲገባ ተደረገ። ከመቀሌ በወያኔ ከተባረረ በኋላ፣ ጌታቸው ረዳ በተፈናቃይ ስም ሚሊሺያ ብቻ ሳይሆን የወያኔ ልዩ ኃይል ጭምር እንደገባ አጋለጠ። የተከዜ ዘብ እስካለ ድረስ ፣ወልቃይት ላይ እንደ ራያ አላማጣ ወያኔ በተፈናቃይ ስም ታጣቂ ይዞ መግባት እንደማይችል ሲያውቅ፣ ተፈናቃዮችን ባሉበት እንዲቆዩ ወሰነ። የአብይም አማራውንና ትግሬውን ዳግም ደም የማቃባት እቅድ ለጊዜው ተሰናከለ።
አሁን ወያኔ ጠለምትን ሲወርና ከአማራው ጋር ውጥረት ውስጥ ሲገባ፣ አብይ ደስታውን መከላከያ ራያ አላማጣንና ኮረምን አንድ ጥይት ሳይተኩስ ለቆ እንዲወጣ በማድረግ ገለፀ። ልክ እንደበፊቱ ሰሜን ሸዋ ድረስ ወረራ፣ አብይ አማራውን ዳግም ለቀጥተኛ ወያኔ ወረራና ውድመት አመቻቸ።
የአማራ ልዩ ኃይል ፈርሶ ከራያና ከወልቃይትም እንዲወጣ የተደረገው ይሄን ለማመቻቸት ነበር። ቢያንስ ለጊዜው ቢሆን የአብይ አማራውንና ትግሬውን ግጭት ውስጥ በመክተት ምኞቱ የተሳካለት ይመስላል ። አማራውና ትግሬ በወልቃይት ጉዳይ ማቆሚያ የሌለው ጦርነት ውስጥ ካልገቡ፣ ስልጣኔ አይረጋም ብሎ አብይ ደምድሟል።
፪. ወያኔ ለምን የወልቃይትን ጦርነት ይፈልገዋል?
አብይ የሚፈልገውን ነገር ሁሉ አግኝቶ ድርድሩ ቢቋጭም፣ የፕሪቶሪያ ስምምነት ቢያንስ የሕወሃት እስትንፋስ ቀጥ እንዳትል ከመርዳት ባሻገር፣ በውስጥ የነበረው ክፍፍል ወደ ውጭ እንዳይወጣ ረድቶታል።
የፕሪቶሪያ ስምምነት በሚጻረር መልኩ፣ በአብይ ፍቃድ የሽግግር ስርዓት በትግራይ በሕወሃት ብቻ ከተመሰረተ በኋላ፣ በህወሃት ውስጥ በአመራሩ መካከል በጦርነቱ ወቅት የነበረው መሰንጠቅ ቀስ በቀስ በግልጽ መታየት ጀመረ።
መጀመርያ የጌታቸው ረዳ ቡድን በአብዛኛው የራያን ተወላጆችን ይዞ ተሰንጥቆ ወጣ። ብዙም ሳይቆይ የታደሰ ወረደ እንደርታ ቡድን ወላዋይ ሆኖ ከአብይም ከህወሃትም ሳይሆን በመሃል ላይ እንደተንሳፈፈ አለ።
የቀረው የደብረጽዮን ግሩፕ እንደገና ወደ ሞንጆሪኖና ስብሃት ነጋ ከኋላ ወደ ሚዘውረው ወደ ዓለም ገብረዋድ በድን ተከፋፈለ። ይሄ ክፍፍል በወያኔ ጦር ውስጥም ተከሰተ። በአብይ የሚደገፍ ትግራይ የሰላም ጦር (TPF) የሚባል በእነ ጻድቃን በበላይነት የሚመራ የኦህዴድ- ሕወሃት ታጣቂ ተመሰረተ። እነ ደብረጽዮን ከኢሳያስ ጋር “ፅምዶ” ሲፈጥሩ ደግሞ፣ በኢሳያስ መዳፍ ውስጥ የወደቀ የሻዕቢያ- ሕወሃት ታጣቂ ተፈጠረ። “በፅምዶ” ምክንያት ከአብዛኛው ህዝብ ጋር ህወሃት ሆድና ጀርባ ሆነ። ባጭሩ ሕወሃት በታሪኩ እንደዚህ እንደ አባ ጨጓሬ ብዙ ቦታ ተሰነጣጥቆ አያውቅም። አንዳንድ የሕወሃት ጄኔራሎች ከሕወሃት በላይ ጥርስ እያወጡ መጥተው፣ ለሕወሃት ከለመታዘዝ ባሻገር፣ ድርጅቱን በእነሱ ተጽዕኖ ስር አዋሉ።
የፕሪቶሪያ ስምምነት እንዳበቃ፣ ከአማራ ይመጣል ብሎ የሰጋውን የስልጣን ፉክክር ለማስወገድ፣ አብይ ሕወሃት ከአማራ ጋር በወልቃይት ጉዳይ ጦርነት እንዲከፍትለት
አሴረ። ስምምነቱ ሕወሃት ትጥቅ ሙሉ ለሙሉ እንዲፈታ ቢያስገድድም፣ አብይ በአንድ በኩል የአማራን ልዩ ኃይል እያፈረሰ፣ ጎን ለጎን በሴራ ሕወሃት ትጥቁን እንዳይፈታ አደረገ።
ከጦርነቱ ጠባሳ ገና ያላገገመው ሕወሃት፣ ወልቃይት ላይ ጦርነት ከመክፈት ይልቅ፣ እንደ ፌዴራል መንግስትነትህ ማድረግ ያለብህን ሁሉ አድርገህ ወልቃይትን አስረክበኝ ብሎ አብይን ይጎተጉት ጀመረ። የሕወሃት ለአብይ ጥቅሙ እዚህ ላይ አበቃ። አብይ ሕወሃትን ህጋዊ እውቅና ነፍጎ ምርጫ ቦርድ እንዲሰርዘው አደረገ።
አሁን ላይ ሕወሃት በታሪኩ በትግራይ ህዝብ ተቀባይነቱ እጅግ በጣም ያሽቆለቆለበት ጊዜ ነው። ዳግም አፈር ልሶ ለመነሳት ወያኔ ወልቃይትን መውረር አለብኝ ብሎ የወሰነ ይመስላል። የትግራይ ብሄረተኞችን በሙሉ አንድ የሚያደርጋቸው ጉዳይ የጎንደር ክፍለ ሀገር መሬት የወልቃይት ጉዳይ ነው። የሰሞኑ የሕወሃት የጠለምት ወረራ የዚህ በትግራይ ህዝብ ተቀባይነት የማግኘትና ዳግም የማንሰራራት ቀመር ነው።
ይሄ የሻዕቢያ- ሕወሃት ጀብደኝነት የት እንደሚደርስ አብረን እናያለን።
የፕሪቶሪያ ስምምነት የህወሃት ነፍስን እንዳተረፈው ሁሉ፣ ወልቃይት ላይ ወያኔ ጦርነት መክፈቱ በትግራይ ህዝብ ያጣውን ተቀባይነት መልሶ ሊያስገኘው ይችላል። የአብይ ወጥመድ ውስጥ ግን ይወድቃል።
ነገር ግን በትግራይ ዋጀራት አሁን በኦህዴድ- ሕወሃትና በሻዕቢያ- ሕወሃት የተጀመረው አዲስ ጦርነት፣ ወያኔ ወልቃይትን የማጥቃት እቅዱን በይደር ሊያቆየው ይችላል። በተጨማሪ የጠለምት ወረራ የጠበቀውን ያህል ድጋፍ ወያኔ ከህዝቡ እስከ አሁን ድረስ ስላላገኘበት፣ ተዋጊውን የያዘውን ቦታ ለቆ እንዲያፈገፍግ አዟል።
፫. የፋኖ አቋም በጉዳዩ ምን ይሁን?
ወያኔ ጠለምትን፣ ራያንና ወልቃይትን እየወረረ ባለበት ሰዓት፣ ፋኖ በዚህ ጉዳይ አያገባኝም ብሎ ዝምታን ሊመርጥ አይችልም። ካለጥርጥር የአማራ ህልውና ትግል ቀይ መስመር እነ ወልቃይት ናቸው።
ፋኖ የወያኔን የወልቃይት ወራራ ችላ ብሎ ወደ አዲስ አበባ ለመሄድ ከወሰነ፣ ከአማራ ህዝብ ጋር እስከወዲያኛው ሊያቆራርጠው ይችላል።
ከአማራጭ ማጣት ፋኖ ከወያኔም ከአብይም ጋር በሁሉት ግምባር ጦርነት ውስጥ ለመግባት ከወሰነ ደግሞ፣ የአብይ ወጥመድ ውስጥ ይገባል።
በተለያዩ መሬት ላይ ባሉ አስገዳጅ ምክንያቶች ፋኖ፣ ኢሳያስና ወያኔ የጋራ ጠላታቸው የአብይ ስርዓት ላይ የጋራ ትብብር ሊያደርጉ ይችሉ ይሆናል። ይሄ ከተሳካ “ሰሜነኞቹ” ተባብረው የኦሮሙማን መንግስት በማስወገድ የአብይን ሴራ ያከሽፋሉ። ነገር ግን ወያኔ ጠለምትንና ራያን ወሮ እስከያዘ ድረስ፣ ይሄ ትብብር የማይጠበቅና የማይገመት ነው። ፋኖ ከአብይ፣ ከኢሳያስና ከወያኔ ወጥመድ በላይ በማሰብ፣ ህዝቡን ከጎኑ ይዞ የአማራውን ህልውና ትግል ከግብ ማድረስና ሀገረ ኢትዮጵያን ማስቀጠል ይጠበቅበታል።
፬. ኢሳያስና ወልቃይት
ወያኔ የሆዱን በሆዱ ይዞ፣ ከኢሳያስ ጋር “ፅምዶ” የፈጠረው መውጫ በር ለማግኘት እንደሆነ ምንም ጥርጥር የለውም። ወደ ሱዳን መሻገርያ ኮሪደር የማግኘት ጉዳይ ወያኔንና ሻዕቢያን ጫካ እየነበሩ በተደጋጋሚ ለጦርነት ዳርጓቸዋል። የወልቃይትም በወያኔ የመወረር ዋና ምክንያት ወደ ሱዳን መውጫ በር ፍለጋ መሆኑን ማስታወስ ተገቢ ነው። በቅርቡ ጦርነት መሸሻ ኮሪደር ማጣት ምን ማለት እንደሆነ ከሕወሃት በላይ የሚያውቅ የለም።
ወያኔ ወልቃይትን በእጁ ከከተተ፣ የኢሳያስ አገልግሎት ያበቃል። ወያኔ የሚፈልገውን እርዳታ በቀጥታ ከግብጽና ከሱዳን በወልቃይት በኩል ያገኛል።
ወደ ሱዳን መውጫ ኮሪደር ወያኔ ካገኘ፣ ጦሩን ወደ ኢሳያስ ሰብቆ ለበቀል እንደሚነሳ ኢሳያስ ይጠፋዋል ብሎ መገመት የዋህነት ነው። ወያኔና ሻዕቢያ ስር የሰደደ ጊዝያዊ ወዳጅነት የማይለውጠው አጥፊና ጠፊ ቡድኖች ናቸው። ስለዚህ ወልቃይት ወያኔ እጅ ላይ መውደቅ ለኢሳያስም ቀይ መስመር ሊሆን የሚገባ ይመስላል።
Opinions expressed by contributors are their own. Ethiofact does not endorse and is not responsible for the accuracy of any of the views expressed in the content on this site.