Afar and Kunama

ከወልቃይት ባሻገር!

በአበራ ገ/ማርያም

እንደ ግለሰብ መለስ፣ እንደ ድርጅት ሕወሃት የትግራይ ህዝብ የዘለቄታ ጥቅም ላይ የሰሩት ከባባድ ስህተቶች አሁን ላይ የተወሰኑ የትግራይ ሰዎች እየገባቸው መጥቷል። በዚህ ከቀጠለ አብዛኛው የትግራይ ህዝብ በጉዳዩ ላይ በቂ ግንዛቤ ለመያዝ ብዙ ጊዜ የሚወስድበት አይመስልም።

መለስ በትግራይ ህዝብ ላይ ከሰራቸው ከባባድ ስህተቶች መካከል ለዛሬ ሁለቱን ብቻ እንፈትሽ።

፩. የወልቃይት/ራያ ከህግ ውጪ በሕወሃት መጠቅለል

ከሚናገሩት ቋንቋ በስተቀር ምንም ልዩነት የሌላቸውን የአማራና የትግራይ ህዝብ፣ ክፉና ደጉን አብረው ያሳለፉ ህዝቦች፣ አንዳቸው የአንዳቸው ቀኝ እጅ መከታ የሆኑ ህዝቦች፤ በወልቃይት/ራያ ጉዳይ መለስ በማን አለብኝነት የወሰደው ኋላቀር አቋም ደም አቃብቷቸዋል። ከሁለቱም ህዝቦች አስተዋይ መሪዎች እስኪወጡ ድረስ በመካከላቸው ያለው ፍጥጫ፣ ውጥረትና ጦርነት ካለጥርጥር ይቀጥላል። የችግሩ ፈጣሪ ሕወሃት የመፍትሄ አካል ሊሆን እንደማይችል ከምንግዜውም በላይ አሁን በወልቃይትና ራያ ላይ እያራመደ ያለው አቋም ግልጽ እያደረገው መጥቷል።

ወልቃይት ከጎንደር፣ ራያ ከወሎ ክ/ሀገር ከህግ ውጪ በነፍጥ ወደ ትግራይ የተወሰዱት እነ መለስ የሽግግር መንግስት ከማቋቋማቸው በፊት፣ ህገ መንግስት/ ህገ ሕወሃት የኢትዮጵያ ህዝብ ላይ ከመጫኑ በፊት መሆኑን የትግራይ ህዝብ ምን ግዜም ልብ ሊለው ይገባል።

በሚኒሊክ/በዮሃንስ/ በጎበና/በጦና ኢትዮጵያ፣ የትግራይ ህዝብ ወደ ድፍን ጎንደር፣ ጎጃም፣ ሸዋ፣ ወሎ፣…ወልቃይትና ራያን ጨምሮ የመኖር፣ የመስራት፣ ሀብት የማፍራት የማይገሰስ መብት ነበረው። ካለምንም ብዥታ መላ ኢትዮጵያ የትግራይ ህዝብ ርስት ነበረች።

ታንክና ባንኩ ከሕወሃት እጅ ከወጣ በኋላ ግን፣ መለስ በፈጠራት በአፓርታይድ ክልሎች/ ባንቱስታኖች በተሸነሸነች ኢትዮጵያ የትግራይ ህዝብ ከትግራይ ውጪ ወደ ሌላ ኢትዮጵያ ግዛት ተንቀሳቅሶ የመኖር፣ የመስራት፣ የመነገድ፣…መብቱ በእጅጉ ተገድቧል። ከአውሮፕላን በረራ ውጪ፣ በአሁኑ ወቅት በየብስ በአፋር በኩል ያውም ሰላሙ አስተማማኝ ያልሆነ ከተራዘመ ጉዞ ውጪ፣ የአሉላ ልጆች ወደ ተቀረው ኢትዮጵያ መምጣት አይችሉም።

የትግራይ ህዝብ ወደ ተቀረው በደሙ ባቀናት አገሩ ኢትዮጵያ ለመኖር ይመጣል እንጂ፣ የተቀረው የኢትዮጵያ ህዝብ ለውትድርና ካልሆነ በስተቀር ወደ ትግራይ አይሄድም። ይሄ መሬት ላይ ያለ ሃቅ ነው።

ከታሪክ እንደምንማረውና መሬት ላይ ያሉ የኢኮኖሚ ህጎች እንደሚያመላክቱት፣ የትግራይ ህዝብ ከትግራይ ውጪ ወደ ተቀረው ኢትዮጵያ ሄዶ መኖር፣ መስራት፣ ሀብት ማፍራት፣…የግድ አለበት።

ሕወሃት ደደቢት እንደተመሰረተው፣ በወልቃይት ጉዳይ ቆሌው ተገፎ፣ ተዋርዶ፣ ድምብርብሩ ወጥቶ፣….ወደ ታሪክነት ለመቀየር በማጣጣር ላይ ይገኛል።

የሕወሃት መንገድ ለትግራይ ህዝብ በፊትም አላዋጣም፣ አሁንም አያዋጣም። የትግራይ ህዝብ ከማናቸውም ነገር በላይ ከአማራ ህዝብ ጋር ሰላም ያስፈልገዋል። ህወሃት ባመጣው ጣጣ ከዘለቄታ ጥቅሙ ጋር ተለያይቶ መቅረት የለበትም። ወልቃይትና ራያ ብቻ ሳይሆኑ እንደበፊቱ መላ ጎንደር፣ ወሎ፣ሸዋ፣ ጎጃም፣…..የትግራይ ህዝብም ጭምር መሆኑን መቀበል የተሻለው አዋጪው መንገድ ነው።

ወልቃይትና ራያ ከህግ ውጪ በነፍጥ በሕወሃት ከጎንደርና ከወሎ ክ/ሀገሮች መወሰዳቸውን ተቀብሎ፣ ከመለስ ስህተት የትግራይ ህዝብ ራሱን በማራቅ፣ ከአማራ ወገኖቹ ጋር እንደገና እጅ ለእጅ ተያይዞ፣ ተደጋግፎ ልክ እንደበፊቱ ለጋራ በእኩልነት የሚኖሩባትን ኢትዮጵያን መመለስ አለባቸው።

፪. ትግራይን ለዘላለሙ አናሳ አድርጎ ያስቀረው የመለስ ህገ መንግስት/ ህገ ህወሃት

አፍቃሪ ወያኔ ጋዜጠኛ ዳዊት ከበደ ስብኃት ነጋን፣ ኢትዮጵያን በመመስረት ትልቅ ድርሻ ያለን ነባር ህዝቦች ሆነን ሳለ፣ አብይ ስልጣን ከያዘ በኋላ ድርሻችሁ እንደቁጥራችሁ ብሎ እዚ ግባ የሚባል ሚና የሌለን አናሳ አድርጎ የትግራይ ህዝብን እስቀርቷል። መፍትሄው ደግሞ መገንጠል ነው ብሎ ላቀረበው ጥያቄ፣ የስብሃት ነጋ መልስ ወልቃይትን ይዤ ልገንጠል ብትል አማራው ይለቅሃል ነበር።

ዳዊትና አፍቃሪ ወያኔዎች እራሳቸውን መጠየቅና መቀበል ያለባቸው ግልጽ ሃቅ ቢኖር፣ ትግራይን እስከ ወዲያኛው አናሳ አድርጎ ያስቀረው ወያኔ የፈጠረው የአፓርታይድ ባንቱስታን ክልሎችና የጎሳ ህገ መንግስት/ ህገ ሕወሃት መሆኑን ነው።

የኦህዴዱ አብይ በአንድ ወቅት እንደተናገረው፣ የሱማሌ ህዝብ ከትግራይ ህዝብ በቁጥር ብልጫ እያለው ፣ በምን መለኪያ ትግራይ ከሱማሌ በላይ 39 መቀመጫ በፌዴሬል ፓርላማ እንዲኖራት ተደረገ ብሎ ጠይቋል። አብይ ወደፊት የፓርላማ መቀመጫ ብዛት መሸጋሸጉ አይቀሬ መሆኑን ጠቆም ማድረጉ ነበር። ከፌዴራል መንግስት ወደ አፓርታይድ ባንቱስታኖች/ ክልሎች የሚደረገው የበጀት ድጎማ የህዝብ ብዛትን ግምት ውስጥ የሚከት ነው የሚሆነው። በዘመነ ኦህዴድ፣ በወያኔ ዘመን ትግራይ ከምታገኘው አንጻር፣ የአሁኑ የፌዴራል ድጎማ እጅግ ዝቅተኛ ነው።

ወልቃይትና ራያ ወደ ባለቤታቸው ወደ ጎንደርና ወሎ ክፍለ ሀገር ሲመለሱ ደግሞ፣ የትግራይ ህዝብ ቁጥር እጅግ በጣም ይቀንሳል።

ይሄ ማለት፣ መለስ በዘረጋው የአፓርታይድ ክልሎች ስርዓት፣ ትግራይ ከሌሎች ድጋፍ ካለገኘች በስተቀር በፌዴራል ፓርላማ ውስጥ አጀንዳ አስይዛ፣ አወያይታ፣ የምታሳልፈው አንዳችም አጀንዳ አይኖራትም። ሁሉም ነገር የሚሆነው አብላጫ ህዝብ ብዛት ባላቸው በብሄረ ኢትዮጵያኖች/ ውህድ ኢትዮጵያኖች፣ በአማራውና በኦሮሞ ፍላጎት ነው። ኦሮ-ማራን ያጤኗል!

ልክ እነ ጋምቤላ የኢህአደግ አጋር እንደነበሩት፣ ትግራይ በቀጥር አብላጫ ላላቸው ለብሄረ ኢትዮጵያኖች (ውህድ ኢትዮጵያኖች) ለአማራው፣ ለኦሮሞው፣ ለሱማሌው፣….አጋር ሆኖ ከማገልገል ውጪ መለስ በዘረጋው ስርዓት አማራጭ የላትም።

መለስ የዘረጋው ስርዓት እስካልተቀየረ ድረስ፣ የትግራይ ውክልና በፌዴራል ሚኒስትርነት፣ በጦሩ፣ በደህንነቱ፣ በፓሊስ፣ በሲቪል ሰርቪስ፣….የትግራይ ህዝብ ቁጥርን ያገናዘበ፣ ዳዊት ከበደ እንደፈራው እዚህ ግባ የማይባል ነው የሚሆነው።

አብይ ወደ ትግራይ ነዳጅ፣ በጀት፣ ደሞዝ፣ መላክ የሚያቆመው፣ ስልክ/ መብራት/ ባንክ እንደፈለገ የሚዘጋው የሚከፍተው፣ ባሻው ሰዓት ትግራይን የጦርነት ሜዳ የሚያደርጋት፣ ….አማራውና ትግሬው ሆድና ጀርባ እስከሆኑ ድረስና ይሄ መለስ የፈጠረው የአፓርታይድ ባንቱስታን እስካለ ድረስ ብቻ ነው።


Opinions expressed by contributors are their own. Ethiofact does not endorse and is not responsible for the accuracy of any of the views expressed in the content on this site.

guest

0 Comments
Oldest
Newest Most Voted
Inline Feedbacks
View all comments

0
Would love your thoughts, please comment.x
()
x